በገዋኔ በፌደራል ፖሊስና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ተጎዱ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ዛሬ ሰኔ 20፣ 2001 ዓም አንድ የአፋር ወጣት በኢሳዎች መገደሉን ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች ሬሳውን በመያዝ ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ፖሊሶች ወደ ሚገኙበት ካፕም ሲያመሩ የፌደራል ፖሊሶች ” ዘወር በሉ” በማለት ሰልፈኞችን ሲጠይቁ፣ ሰልፈኞችም ” ጥያቄያችን  ሳይመለስ አንሄድም” በማለታቸው  ተኩስ እንደተከፈተባቸው እና ሁለት ሰዎች እንደቆሰለባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሞቱ ሰዎች እንዳሉ የተጠየቁት የአካባቢው ነዋሪዎች ፖሊሶች ሊያስጠጉን ስላልቻሉ ለማወቅ አልቻልም የሚል መልስ ሰጥተዋል። ከቆሰሉት መካከል አንዱ ሆዱን ሌላው ጭንቅላቱን መመታታቸው ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው የመሳሪያ ፍተሻ እናደርጋለን በማለታቸው ከወረዳው ፖሊሶች ጋር መጋጨታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በገዋኔ አካባቢ በአፋር እና በፌደራል ፖሊሶች መካከል የሚታየውን ተደጋጋሚ ግጭት በተመለከተ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።