ምርጫ ቦርድ “ቀኝ እጆቼ” ለሆኑት የምርጫ አስፈጻሚዎች የምከፍለው ገንዘብ አጣሁ ሲል አቤቱታ አቀረበ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበጀት ችግር ምክንያት ለምርጫ አስፈጻሚዎች እና የህዝብ ታዛቢዎች የድጎማ ገንዘብ ባለመክፈሉ ምክንያት በቀጣዩ ምርጫ ላይ ሥጋት እንዳጠላበት ለፓርላማው ይፋ አደርጓል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና  ለፓርላማው ባቀረቡት የ2005 አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በ2005 ዓ.ም የአካባቢ፣ የአዲስአበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫ ማስፈጸሚያ በድምሩ ከ184 ሚሊየን ብር በላይ የተፈቀደለት ቢሆንም የተጠየቀው በጀት ሙሉ በሙሉ ባለመለቀቁ ምክንያት ለሁለተኛ ዙር ምርጫ አስፈጻሚዎች እና የሕዝብ ታዛቢዎች ድጎማ መክፈል አልተቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎቹ ተቀይመው በቀጣዩ የ2007   ጠቅላላ ምርጫ ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማምጣታቸው እንደማይቀር ቦርዱ ማመኑን በመግለጽ ችግሩ እንዲፈታ ፓርላማውን ተማጽነዋል፡፡

በጠቅላላው 250ሺ ምርጫ አስፈጻሚ እና 250 ሺ የሕዝብ ታዛቢዎች ለአዲስአበባና ለድሬዳዋ መኖራቸውን የጠቀሱት ፕ/ር መርጋ ፣ በበጀት እጥረት ምክንያት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ክልሎች ከሚኖሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች በስተቀር ሌሎች ክፍያ አላገኙም ብለዋል፡፡ ” ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነን፡፡ ምርጫ አስፈጻሚና የሕዝብ ታዛቢዎች ደግሞ ቀኝ እጆቻችን ናቸው፡፡ ወደ 54 ሚሊየን ብር ገደማ ለክፍያ ያስፈልገናል” ሲሉ ፓርላማውን ተማጽነዋል፡፡

ቦርዱ የሚመደብለትን በጀት በአግባቡ ይጠቀምበት እንደሆነ ለተነሳላቸው ጥያቄም ፣  ችግር መኖሩን በመግለጽ መልሰዋል።

ፕ/ር መርጋ ” ቦርዱ ስራ የጀመረው የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ ነው፡፡ ስራ ስንጀምር የዲግሪ ምሩቅ ባለሙያዎች  አምስት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ይህን ለማስተካከል ቦርዱ አቅጣጫ ሰጥቶ የየዕለት ስራ ውስጥ በመግባት ጭምር ለማስተካከል ብዙ ሰርቷል፡፡ ቀድሞ በ100 ሚሊዮኖች አይወራረድም ነበር፡፡ አሁን ግን ቢበዛ ከ10 ሚሊየን ብር አይበልጥም በማለት በብር መጠን ያሳየውን መሻሻል ለፓርላማው” ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ለ10 የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና በክልል ም/ቤቶች ባላቸው መቀመጫ ብዛት ልክ ለዕለት ተዕለት ስራ ማከናወኛ 20 ሚሊየን ብር አስፈቅዶ 8 ፓርቲዎች መቀበላቸውን ፕሮፌሰሩ  በሪፖርታቸው የጠቀሱ ሲሆን ማን ምን ያህል እንደወሰደ ሳይገልጹ አልፈውታል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ አንድ የፓርላማ አባል ፣ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ 570/2000 መሰረት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ በዝርዝር ለፓርላማው ሪፖርት እንደሚደረግ በመጥቀስ፣  ዝርዝሩ ለምን እንዳልቀረበ ያነሱትን ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ሳይመልሱት ቀርተዋል፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ  በበኩላቸው መድረክ ከቦርዱ ለዕለት ተዕለት ስራ ማስኬጃ 3 ሺ ብር ተመድቦለት ተመላሽ እንዳደረገ በመግለጽ ኢህአዴግ ግን የሚሰጠውን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በም/ቤቶች መቀመጫ ለሌላቸው ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ በኩል እንደሚያከፋፍል ከገለጹ በሁዋላ፣ ግንባሩ ይህን ድርጊት በማን ፈቃድ እንደሚያከናውንም ጠይቀዋል። የምርጫ ቦርዱ ሀላፊ ግን ለዚህም  ጥያቄ መልስ ሳይሰጡ ዘለውታል፡፡

ዶ/ር መርጋ ” በአሁኑ ወቅት በጠቅላላው 76 ፓርቲዎች መኖራቸውን እና ወደ 6 ያህል ፓርቲዎች መሰራዛቸውን ለአንዱ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፣ 54 ያህል ፓርቲዎች በከፊል ሪፖርት ማድረግ ያለባቸውን ያላደረጉ መሆኑን” ተናግረዋል፡፡