ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በገርባ የፌደራል ፖሊስ አባላት 2 ሰዎችን ረሸኑ፣ የሟቾች ቁጥር 4 ደርሷል :: የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የማቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ይላሉ
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በገርባ ቀበሌ በትናንትናው እለት የወረዳው ፖሊስ አባላት ሆን ብለው በጫሩት ግጭት 4 ሰዎች ሲገደሉ 2ቱ በልዩ ሀይሎች ተወስደው መረሸናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኢሳት ዘጋቢ የተለያዩ የአካባቢው ነዋሪዎችን አነጋግሮ ለማረጋገጥ እንደቻለው 2ቱ ሰዎች ማለትም ሼህ ሁሴን እና አቶ ሰይድ አብደላ የተባሉት ሰዎች በገርባና በባቲ መካካል በመትገኘዋ ዱሪ ከተማ ላይ ሁለቱም አንገታቸው አካባቢ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል። ሁለቱ ግለሰቦች በፌደራል ፖሊስ አባላት ከተያዙ በሁዋላ በመኪና ተጭነው ወደ ባቲ መወሰዳቸውን፣ መንገድ ላይም እንደተረሸኑ፣ ፖሊሶችም የአካባቢውን ሰዎች ጠርተው ” ሁለቱ ሰዎች መንገድ ላይ ሞተውብናልና መጥታችሁ ውስዱ” በማለታቸው ህዝቡ ወደ ቦታው ሄዶ እንዳመጣቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች በተያዙበት ወቅት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የአካባቢው ሰዎች አስረግጠው የተናገሩ ሲሆን፣ አስከሬናቸው መስጊድ ላይ ተወስዶ ሲታይ ሁለቱም ከአንገታቸው አካባቢ መመታታቸውን ህዝቡ ለማረጋጋጥ መቻሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ሼህ ሁሴንና አቶ ሰይድ አብደላን ዛሬ ለመቅበር ችሎአል ።
በእለቱ ከገርባ ቀበሌ ወጣ ብለው በሚገኙ የገጠር መንደሮች የሚኖሩ 2 ሰዎችም ተገድለው አስከሬናቸው ተወስዷል።
ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን አንደኛው የተገደለው በገጀራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በድንጋይ መሆኑን የአካባቢው ሰዎች ጨምረው ገልጠዋል። አንደኛው የፌደራል ፖሊስ የተገደለው በህዝቡ ላይ የወረወረውን አስለቃሽ ጭስ ሌላ ወጣት በመያዝና መልሶ ወደ ፖሊሱ በመወርወሩና ፖሊሱም አከታትሎ በመተኮስ ወጣቱን በመግደሉ ነው። የወጣቱን መመታት የተመለከቱት ነዋሪዎችም ወታደሩን በመክበብና መሳሪያውን በመቀማት በሰደፍ ደብድበው ፖሊሱን ገድለውታል።
በእለቱ በተነሳው ግጭት 10 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን 5ቱ በደሴ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል። አብዛኞቹ ቁስለኞች በህዝብ ማመላለሻ መኪና ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ናቸው።
እንዲሁም 5 ወጣቶች፣ 2 ህጻናትና 2 አዋቂዎች እስካሁን የደረሱበት ባለመታወቁ ቤተሰቦቻቸው ፍለጋ ላይ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ትናንት ምሽት መብራት በማስጠፋት የሚፈልጉዋቸውን ሰዎች ለመውሰድ መኩራ አድርገው እንደነበር፣ ይሁን እንጅ ህዝቡ በንቃት ሲጠብቅ በማደሩ ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ታውቋል።
የልዩ ሀይል አባላት የመስጊዱን ኡስታዝ ሼህ አሊን ለመያዝ ሙከራ ቢያደርጉም ህዝቡ ግን ኡስታዙን በመደበቁ ሊያዙ አልቻሉም።
ዛሬ ጧት የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካካቢው ቅኝት ሲያደርጉ ከዋሉ በሁዋላ ፣ ከከተማዋ በመውጣት በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች ሰፍረዋል። በከተማው ውስጥ ያሉ መለስተኛ ንግድ ሱቆችና ሻሂ ቤቶች በሙሉ ተዘግተዋል።
መንግስት ሶስት ነዋሪዎችና አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል መገደላቸውን መግለጡ ይታወሳል። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከ4 በላይ ነው በማለት ይናገራሉ።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከተሾሙ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወሰዱት የመጀመሪያው የግድያ እርምጃ በገርባ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግስት ስልጣን ከያዙ በሁዋላ የወሰዱት የመጀሪያው ግድያ እርምጃ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ እንደነበር ይታወሳል።