ህዳር ፲፱(አስራ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግለሰቡ የተገደለው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ ገዳዮችም ከመንግስት ጋር ባላቸው ቅራኔ የተነሳ ጫካ የገቡ ሰዎች ናቸው ተብሎአል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘነው መረጃ መሰረት በጅማ ዞን ኪሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው በለጣ ጫካ ውስጥ በመደበቅ አልፎ አልፎ ጥቃት የሚሰነዝሩ የአኮረፉ ነዋሪዎች ቻይናዊውን የገደሉት ፎቶ ግራፍ ለማንሳት በሚሞክረበት ወቅት ነው።
ቻይናዊው የመንገድ ሰራተኛ ግለሰቦችን በጫካ ውስጥ ሆኖ እንዳያቸው ፎቶ ማንሳት መጀመሩን የሚናገሩት ምንጮች፣ ቻይናዊው ባልጠረጠረበት ሁኔታ አንድ ግለሰብ ከጀርባ በመምጣት ወግቶ ገድሎታል ብለዋል። በሁኔታው የተበሳጨው መንግስት የጦር ሄሊኮፕተር ወደ አካባቢው በመላክ ሳምንቱን ሙሉ በለጠ ጫካን ሲያስስና ነዋሪዎችን ሲያሸብር መሰንበቱ ታውቋል። ቀደም ብሎ ኦነግ በአካባቢው ሲንቀሳቀስ ቢቆይም የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት ተደጋጋሚ ጥቃት ግንባሩ አካባቢውን እንደለቀቀ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በመንግስት ትንኮሳ እንዳኮረፉ የሚነገርላቸው እነዚህ ሰዎች መኪኖችን እያስቆሙ የሚፈልጓቸውን እቃዎች እንደሚወስዱም ታውቋል። የአካባቢው ባለስልጣናት ወደ ስራ ሲሄዱም በአጃቢዎች ካልሆነ ብቻቸውን አይጓዙም።
መንግስት ተቃዋሚዎች ናቸው ብሎ የጠረጠራቸውን በሙሉ በማሰር ላይ ሲሆን ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ አሰሳውን አለማቆሙ ታውቋል።
በለጠ ጫካ በደርግ ጊዜ የተተከሉ ራጃጅም ጽዶች የሚገኙበት ሰፊ ጫካ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር የጅማ ዞን ፖሊስን አዛዥን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። መንግስት ስለተገደለው ቻይናዊ እስካሁን ይፋዊ መረጃ አልሰጠም።