(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2011)በድሬዳዋ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉ ተሰማ።
የተጠራቀመውን ብሶትና በደል ለመግለጽ አደባባይ የወጣው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር መጋጨቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የከተማው መዋቅር ነዋሪውን ባይተዋር ያደረገ፣ መብትና ጥቅሙን የገፈፈ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
ህዝቡ ንብረት ከማውደምና ከማቃጠል ተቆጥቦ ጥያቄውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲገልጽም ጥሪ ተደርጓል።
የተቃውሞ ትዕይንቱ ላይ የከተማው ከንቲባ ከስልጣን እንዲወርዱ ተጠይቋል።
ዛሬም መንገዶች በድንጋይና በተቃጠሉ ጎማዎች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማም ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በዛሬው ተቃውሞ የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጢስ መጠቀማቸውም ታውቋል።
ይህን በተመለከተም የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ዑስማን ለኢሳት ምላሽ ሰጥተዋል።