በሶማሌ ክልል 46 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ ሊደረጉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2011) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሶማሌ ክልል በተፈጸሙ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ 46 ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ከእነዚህም 6ቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

የተቀሩት 40ዎቹ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ተሸሽገው እንደሚገኙም አስታውቋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉና በቀጥታ ትዕዛዝ የሰጡት የሶማሌ ክልል የቀድሞ አመራሮች ላይ የተጀመረው ህጋዊ ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው አቃቤ ህግ የተሸሸጉትን ተጠርጣሪዎች ህዝቡ አሳልፎ እንዲሰጥም ጠይቋል።

ከሃገር የወጡትንም ከያሉበት ሃገር መንግስት ጋር በመነጋገር ለህግ ለማቅረብ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የፊዴራሉ አቃቤ ህግ እንዳለው በሶማሌ ክልል በቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር በሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወንጀል  ምርመራ ገና አልተጠናቀቀም።

ይህም ሆኖ ግን እስካሁን በተደረገው ምርመራ በርካከታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን አቃቤ ሕግ አረጋግጧል።

አቃቤ ህግ እንዳለው በክልሉ ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ የተገደሉ ሰዎች በርካታ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ከጅቦች እና ሌሎች አራዊቶች ጋር አብሮ የማሰር እና ሌሎች አሰቃቂ ግፍ እና በደል ይደርስባቸው እንደነበርም በምርመራ መረጋገጡን ነው የፌዴራሉ አቃቤ ህግ የገለጸው፡፡

የክልሉ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች ላይ እንዲያምፅ እና በደል እንዲፈፅም በአካል እና በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ ተደርጓልም ነው የተባለው፡፡

የፌደራሉ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌን ጨምሮ የህዝብ እና መንግስት ኃላፊነት ኖሯቸው ይህን ወንጀል በማቀነባበር እና በቀጥታ በመሳተፍ የተጠረጠሩ 46 የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡

ክሱ የተመሰረተውም በዋናነት አስገድዶ በመድፈር፣ህገ-መንግስት እንዲጣስ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና በቀጥታ በመሳተፍ እና በሌሎችም ወንጀሎች ነው ብሏል፡፡

እንደ አቃቤ ሕጉ ገለጻ በዚሁ ወንጀል ከተጠረጠሩት መካከልም ስድስቱ በህግ ቁጥጥር ስር ቢውሉም የተወሰኑት  በውጭ ሃገር ይገኛሉ ፡፡

ይሁን እንጂ ያሉበት ሃገር ስለሚታወቅ እና ከሀገራቱ መንግስታትም ጋር ስምምነት እየተደረሰ ስለሆነ በቅርቡ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥም እያሉ ያለመከሰስ መብት ያላቸው የቀድሞ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አቃቤ ህግ አስታውቋል ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሰጠው መግለጫ ለሰዎች ሞት፣ለአካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ለንብረት ውድመት እና ሌሎች ወንጀሎችን በፈጸሙ አካላት ላይ ተጨማሪ ምርመራ ይደረጋል፡፡