ታህሳስ 08 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በዱባይ የመንግስት ተወካዮች ለህዳሴዉ ግድብ ማሰገንቢያ የሚሆን ያደረጉት የገቢ ማሰባሰቢያ ስብሰባ የተሳካ አለመሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመለከተ
ባለፈው ቅዳሜ ዲሰምበር 17/2011 በዱባይ ከተማ መራቅባት አካባቢ በሚገኘዉ የማርየት ሆቴል ውስጥ በአንድ የኢህአዴግ ሚንስትር ዴኤታ የሚመራ የተወካዮች ቡድን ለህዳሴዉ ግድብ ማሰገንቢያ የሚሆን ስብሰባ ጠርተው የነበረ ቢሆንም፣ ስብሰባውን ወደ 100 ሺህ ኢትዮጵያዉያን ይኖሩባታል ተብሎ በሚታሰበው የአረብ ኢምሬትስ፣ ከ100 ያነሱ ሰዎች መገኘታቸው ታውቋል።
የስብሰባው አጀንዳ በዲያስፖራ ፖሊሲ እና በአባይ ግድብ ዙሪያ እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከውይይቱ በሁዋላ ለተሰብሳቢው የጥያቄ ዕድል የተሰጠ ሲሆን ተሰብሳቢዎችም ” ለምን መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ ይገባል፣ በሀገር ዉስጥ የለው ፍትህ ማጣት ነው ዋናዉ ቁልፍ ነገርና ትኩረት አልተሰጠውም፣ መንግስት የህዝቡን ባህልና ሀይማኖት ከቁብ ሳይቆጥር ለምን የግብረሶደማዉያን ስብሰባ በሀገር ውስጥ እንዲደረግ ፈቀደ፣ ኢትዮጵያዉያን በአረብ አገራት አጅግ ዘግናኝ ግፍ ስደርስባቸዉ አገዛዙ አድም ነገር ሳያደርግ ቆይቶ አሁን ገንዘባችሁን አምጡ ሲል አያፍርም ወይ ፣የሌሎች አገር ዜጎች በሀገራቸዉ የተለየ ክብርና እንክብካቤ ሲደረግላቸው እኛ ግን በሀገራችን ከኤርፖርት ጀምሮ የሚደርስብን እንግልትና መከራ አሳፋሪ ነዉ ለምን? ፤ በአሁን ሰአት እናንተ አደግን አደግን ትሉናላችሁ እድገቱ የት ነዉ ያለው? እናንተ አደግን ትላላችሁ ግን አብዛኛዉ ኢትዮጲያዊ ያለው እኛ በምንልክለት ብር መሆኑን እንዴት ዘነጋችሁት? እኛ ብር መላክ ብናቆም ምንያህል ሰው ጦም እደሚያድር ቤቱ ይቁጠረዉ ቤተሰቦቻችን እኮ እባክሽ ብር ላኪና እኛም እንምጣ ነው የሚሉት፤ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጲያ ዉስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መከፋፈል እና እርስ በእርስ የመጠላላት ሁኔታ ተፈጥሮአል። ማንኛዉም ሀገር እንዲያድግ ከተፈለገ ህዝቡ አንድነት ሊኖረው ይገባል፣ ያለአንድነት እድገትና ሰላም አይኖርም፣ ይህ መንግስት ግን ህዝቡን ከፋፍሎታል ለምን? የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የመድረኩ ሰብሳቢ በመሀል ገብቶ ከዚህ በላይ ጥያቄ አናስተናግድም በማለቱ ተሰብሳቢዉ በሁኔታዉ ተናዶ ሲጮህ ተስምቷል።
ሰብሳቢዉ ጥያቄዎቹ ከአጀንዳው ውጭ ናቸዉ ግን ከተነሱ አይቀር ብዥታ እንዳይኖር ላጥራዉ ብለው ለጥያቄው መልስ ከመስጠት ይልቅ ስለ ህገመንግስቱ መተረክ ጀመሩ።
በዚህ ጊዜ የተበሳጨው ተሳታፊ በያለበት ማውካካትና መጮህ ሲጀምር፣ ሰብሳቢዉም በተለሳለሰ ሁኔታ “እኛ በሀይማኖት መሀል ጣልቃ አንገባም የሙስሊም ካውንሰል ነው አስተማሪዎችን ከሊባኖስ አስመጥቶ ያስተማረው” በማለት መልሰዋል።
ተሰብሳቢዉ የበለጠ በመቆጣት “የእስልምናውን ምክር ቤት እናንተ ያቆማቹት አይደለም እንዴ? እኛ ሙስሊሞችን ፈፅሞ የማይወክል ነው ” በማለት በጩህት አዳራሹን በጠብጦአል።
በስብሰባው አካሄድ ያልተደሰተው ተሰብሳቢ በብዛት አዳራሹን ጥሎ ወጥቷል።
የኢህአዴግ ተወካይ ስለ ግብረሱዶማዉያን ስብሰባ ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ ” እነዚህ ሰዎች ስብሰባ ለማድረግ የጠየቁት የሆቴል ባለቤቶች ስላልፈቀዱላቸው በተ.መ.ድ. ፅ/ቤት አዳራሽ ኦፊሺያል ያልሆነ ስብሰባ አድርገዋል፣ መንግስትም ቢሆን በተ.መ.ድ. ፅ/ቤት አዳራሽ ገብቶ የማስቆም ስልጣን የለውም መልስ ሰጥተዋል።