ጥቅምት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ በደጋንና በገርባን የተነሳውን የሙስሊሞች ተቃውሞ ተከትሎ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን፣ ግጭቱን አስነስተዋል የተባሉ 2 ሰዎች በፌደራል ፖሊሶች እንዲረሸኑ፣ ሌሎች ሁለቱ ደግሞ በግጭቱ ላይ በፌደራል ፖሊሶች ጥይት እንዲገደሉ መደረጉን ፣ ይህን ተከትሎም የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው በስፋት በመስፈር አካባቢውን የጦር ቀጣና እንዳስመሰሉትና እስካሁን ድረስ ከ200 በላይ ወጣቶችን፣ አዛውንቶችንና ሴቶችን ሳይቀር ይዘው ማሰራቸውን የአካባቢውን ሰዎች በማናገር መዘገባችን ይታወሳል።
የአይን እማኞች ዛሬ ለኢሳት እንደተናገሩት ከሆነ በተያዙት ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ እጅግ ዘግናኝ ነው። በርካታ እስረኞች በዱላ ተደብድበዋል፣ አንዳንዶችም መረጃ አውጡ እየተባሉ በሰለጠኑ ውሾች ተነክሰዋል። ከመንገድ ላይ እየታፈሱ የሚያዙት ወጣቶች ህዝቡ እንዳዳያቸው በአምቡላስ መኪና በሽተኞች እየመሰሉ እየተጫኑ ትራንስፖርት ወደ ሌለባቸው ቦታዎች እየተወሰዱ በአጋዚ ወታደሮች እየተደበደቡ ነው። እድል ያጋጠማቸው ወጣቶች ወደ ጅቡቲና የመን መሰደዳቸው ታውቋል። አግአዚ እየተባለ የሚጠራው ጦር ሀርቡ፣ ከምሴ፣ ደጋንና ገርባ ላይ መስፈሩም ታውቋል፡፡
ኢሳት በደጋን አካባቢ የተፈተጠረውን ችግር በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።
ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት አንድ የአካባቢውን ወጣት አግኝተን ስላለው ሁኔታ አነጋግረነዋል