የፌደራል ገቢዎች ባለስልጣን የፍትህ ጋዜጣን አሳታሚ ንግድ ፍቃድ አላድስም አለ

ጥቅምት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፌደራል ገቢዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤት የንግድ ፈቃድ ፈቃድ ለማደስ የሄዱትን የማስተዋል የህትመት ማስታወቂያ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ እና ስራ አስፈጻሚ አባላት የንግድ ፈቃድ አላድስም በማለት እንደመለሳቸው ምንጮቻችን አስታውቀዋል።

ላለፉት 4 አመታት በሀገሪቱ ላይ ያለውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተግዳሮቶች ተቃውሞ ፍትህ ጋዜጣን በማሳተም ለንባብ ሲያበቃ የነበረው ድርጅት ፍቃዱን እንዳያድስ ከበላይ አካል ትእዛዝ እንደወረደ የጠቀሱልን የዜናው ምንጮቻችን አሁንም የበላይ አካል ካለፈቀደ ለማደስ እንደሚቸገሩ የገለጡ ሲሆን እንደ ምክንያት ያደረጉትም የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች አዲስ ታይመስ የተባለውን መጽሄት በፍትህ መንፈስ እያዘጋጁ መሆኑን ነው።

ፍትህ ጋዜጣ ከሀምሌ 3 ቀን 2004ዓም ጀምሮ ህትመቱን እንዲያቋርጥ በመደረጉ ጋዜጣው ስርጭቱን ማቆሙ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት ለመግለጽ ከማይቻልባቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የአፍሪካ  አገሮች መካከል ትጠቀሳለች።