በደብረማርቆስ የሰማያዊ እጩ ተወዳዳሪ ተገደለ

ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃያዎቹ መጨረሻ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ጸሃፊ ሳሙኤል አወቀ ሰኔ 8/2007 ዓም ምሽት ላይ ሁለት ግለሰቦች ወደ ቤቱ ሲገባ ጠብቀው
በፈጸሙበት ድብደባ ህይወቱ አልፎአል።
የሳሙኤል ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች ድርጊቱን የመንግስት ሃይሎች እንደፈጸሙት ምንም ጥርጣሬ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ሳሙኤል ጀግና እና ለአገሩ የሚቆረቆር ጠንካራ ወጣት ነበር የሚሉት ጓደኞቹና የትግል አጋሮቹ፣ በተፈጸመው ድርጊት
ልባቸው መነካቱን ገልጸዋል።
የሳሙኤል የግል ጓደኛ የሆነው አዲሱ ጌታነህ ፣ ድብደባው የተፈጸመው መብራት ጠፍቶ በመሆኑና ድብደባው ከተፈጸመ በሁዋላ መብራት መምጣቱ ድርጊቱ የተቀነባበረ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግሯል።
ባለፈው እሁድ ከሳሙኤል ጋር አብሮ ማሳለፉን የገለጸ አንድ ሌላ የፓርቲው አባልና የቅርብ ዘመድ ፣ ሳሙኤል ተደጋጋሚ ዛቻዎች ሲደርሱት እንደነበርና እየተከታተሉት መሆኑን እንደገለጸለት ተናግሯል። ” እኔ እንዲህ ሆንኩ ብየ በመናገር
ትግሉን መጉዳት ስለማልፈልግ ከእንቅስቃሴ ወደ ሁዋላ አልልም፣ እስከመጨረሻውም እታገላለሁ” እንዳለውም የትግል አጋሩና ዘመዱ ተናግሯል።
ሳሙኤል ከሁለት ሳምንት በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ለደብረማርቆስ ህዝብ የሚከተለውን ጥሪ አቅርቦ ነበር ” ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች! ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ከ25 0000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም
በ31 ዩኒቨርስቲ የምትገኙ ከ14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም። የማያፍረው ብአዴን / ኢሕአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ
ቆጭቷቸው እሰር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሀሰት ክሰ እየፈጠሩ ነው! በስልኬ እደተደወለም ያለፍላጎቴ ደሕንነት እያስገደደኝ ይገኛል፡፡ ተገደልሁም፣ ታሠርሁም፣ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት
የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ፡፡ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ
ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው፡፡ ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም! ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን
ዘላለማዊ ነው! ”
ሳሙአል ከኢሳት የሰብአዊመብቶች ዝግጅት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ከዚህ ቀደም ደርሶበት ስለነበረው ድብደባ እንዲህ ብሎ ነበር ። በሳሙኤል አወቀ አሟሟት ዙሪያ የከተማውን ፖሊስ አዛዥ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።
የሳሙኤል አስከሬን ወደ ትውልድ ቦታው ደብረወርቅ ከተማ መወሰዱ ታውቋል።