አንድ የአረና ፓርቲ አባል ተገደሉ

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአረና ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው አምዶም ገብረስላሴ በፌስ ቡክ ገጹ እንደጻፈው ፣ የ48 አመቱ አቶ ታደሰ ኣብርሃ የተባሉ የዓረና-መድረክ ኣባልና የምዕራባዊ ዞን የዓረና ኣመራር ኣባል ትናንት ማታ 09 / 10 / 2007 ዓ/ም በሶስት ሰወች ታንቀው ተገድለዋል።
አቶ ታደሰ ኣብራሃ በቓፍታ ሑመራ ወረዳ ማይካድራ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በዘንድሮው ምርጫ ወቅት በቀበሌው ኣስተዳዳሪዎች፣ ካድሬዎች፣ የሚቀርቧቸው ሰዎች ከዓረና-መድረክ ኣባልነታቸው እንዲለቁ እየተሸመገሉ፣ የእተለመኑና በመጨረሻም ዛቻዎች ሲደርስባቸው ነበር ሲል አምዶም ጽፏል።
አቶ ታደሰ ከምሽቱ 3 ሰአት ላይ በ 3 ሰዎች አንገታቸውን የታነቁ ሲሆን ፣ ገዳዮቹ ህይወቱ አልፏል ብለው ትተዋቸው ቢሄዱም፣ ህይወታቸው እስከ 09:15 አለማለፉንም ገልጿል። ኣቶ ታደሰ ኣብራሃ የ48 ዕድሜ ጎልማሳ ነበሩ።
የአቶ ታደሰን አስከሬን በሑመራ ሆስፒታል ለማስመርመር ሙከራ ቢደረግም የማይካድራ ፖሊስ ትራፊክ እና የመንግስት ባለስልጣኖች መከለክላቸውን በዘገባው ተመልክቷል።
አረና ባለፈው ታህሳስ ወርም አንድ አባሉን በግደያ አጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወጣት ሳሙኤል አሟሟት ዙሪያ መንግስት የሰጠው መግለጫ ብዙዎችን አስቆጥቷል። መንግስት አንደኛው ገዳይ መያዙን ገልጾ፣ ግድያው የተፈጸመው ከሟቹ የህግ ስራ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ቁርሾ ነው ብሎአል። ይሁን እንጅ ሟቹ ከጸጥታ ሃይሎች ተደጋጋሚ ዛቻ እየደረሰበት መሆኑን አስቀድሞ በመግለጹና በቅርቡም በተፈጸመበት ድብደባ ከሞት መትረፉ፣ ድርጊቱ በኢህአዴግ ደህንነቶች የተፈጸመ ለመሆኑ እንደማያጠራጥር ብዙዎች አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።