ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፖሊሶቹ ዝርፊያ ስለመፈፀማቸው ምስክርነት የሰጡ 18 የ አካባቢው ነዋሪዎችም እንዲታሰሩ ተደረገ።
እንደ ፍኖተ-ነፃነት ዘገባ፤ ፖሊሶቹ ሕዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም በግብርና ሙያ በሚተዳደርና አቶ ለጊዜ ወርቅማ በተባለ የገሊላ ወረዳ ነዋሪ ላይ ዝርፊያ ሲፈጽም ከፍተኛ የ አካል ጉዳት አድርሰውበታል።
ከማሳው ቡና ለቅሞ ወደ ቤቱ እየሄደ ሳለ በወረዳው በሚገኙ የመንግሥት ፖሊሶች ዝርፊያና ከፍ ያለ ጉዳት የደረሰበት አቶ ለጊዜ ወርቅማ፤ በማግስቱ ሕዳር 13 ቀን 2004 ዓ.ም ለሕክምና ዕርዳታ ሄዶ ሕይወቱ አልፏል፡፡
በአቶ ለጊዜ ወርቅማ ላይ ፖሊሶቹ ዝርፊያና ጉዳት ሲያደርሱ አይተናል ያሉ 18 ምስክሮችም፤በሰጡት ምስክርነት ሳቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የታሰሩት ምስክሮች ከዚህ በፊት የቀድሞው የቅንጅት ፓርቲ ደጋፊ የነበሩ መሆናቸውም ተመልክቷል። ከታሳሪዎችም መካከል አቶ አብሪ አየለ፣ካሱ ገመዳ፣ አቶ አየለ ባቢላሮ፣አቶ ከበደ ወርቅማ፣አቶ ዋጃ ዳውካ፣ወ/ሮ ዘነበች ፎርጫና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት የወረዳው አስተዳደር ኃላፊ ወደሆኑት ወደ አቶ ታፈሰ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በመደወል የተደረገው ጥረት አቶ ታፈሰ ፦”ስብሰባ ላይ ነኝ” በማለታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡