የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ኃላፊዎች፤ የፌዴራል ፍርድ ቤት አያዘንም ማለታቸውን ሪፖርተር ዘገበ

ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለመሠረተው የፍትሐ ብሔር ክስ- ማስረጃ እንዲልኩ ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሳቸው የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአውሳ ዞን መስተዳድርና የሚሌ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፦ ‹‹ክሱ መታየት ያለበት በክልላችን በመሆኑ ኃላፊዎችንም ሆነ የምርመራ መዝገቡን ለመላክ ፈቃደኛ አይደለንም›› ማለታቸውን ፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስታወቋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ ፣ ፍርድ ቤቱ በአፋር ክልል የሚገኙትን የፖሊስ ኮሚሽን፣ የዞን ፖሊስና የሚሌ ወረዳ ኃላፊዎችን ከነምርመራ መዝገቡ ይዞ እንዲያቀርብ ታዞ የነበረ ቢሆንም፤ እንዲቀርቡ የተጠየቁት አካላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማስፈጸም አለመቻሉን ዳይሬክቶሬቱ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደንበኛ የሆነው “ሞድ ኢምፔክስ” ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፤ 1 ሺህ 950 ኩንታል ኑግ ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ ወደብ ያጓጉዛል፡፡
የተጫነው ኑግ እስከሚራገፍም ለሚደርስበት ማንኛውም አደጋ ለመሸፈን ዋስትና ይገባል፡፡ ተሽከርካሪው በጉዞ ላይ እያለ ሚያዝያ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. ሦስተኛ ተከሳሽ በሆነው ጀማል ሁሴን አሽከርካሪነት ሚሌ ጉምሩክ ፍተሻ ሲደርስ ተሽከርካሪው ተገልብጦ 11 ቶን ኑግ ወንዝ ውስጥ ይገባል፡፡ አደጋውን ተከትሎ ከፊሉ ኑግ ከአሸዋ ላይ በአካባቢው ነዋሪዎቹ ሲወሰድ፤ ቀሪው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ፣ ከሳሽ የሆነው የመድን ድርጅት አጠቃላይ ለጎደለው ከ390 ኩንታል ኑግ 110 ኩንታል ኑግ ለደንበኛው “ሞድ ኢምፔክስ” ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፤137 ሺህ 874 ብር ከ29 ሳንቲም ከፍሏል፡፡
መድን ድርጅት ያወጣውን ወጭ እንዲከፍሉት ስታር ኢንተርናሽናል የጭነት ባለተሽከርካሪዎች ማኅበርን፣ የተሽከርካሪው ባለቤት የሆኑትን ወ/ሮ ነሲባ ያሲንን እና አቶ ጀማል ሁሴን ይከሳል፡፡
መድን ድርጅት ላቀረበው ለዚህ ክስ ፤መኪናው ሲገለበጥ በቦታው ተገኝቶ መረጃ የሰበሰበው የአፋር ክልል ፖሊስ ማስረጃ እንዲሰጥ ነው የፌዴራል ፍርድ ቤት የጠየቀው።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የወረዳው አስተዳዳሪዎች ግን ጉዳዩ የክልላችን ነው ባዮች ናቸው፡፡
ፌዴራል ፖሊስ ጉዳዩን እንዲያስፈጽም ወደ ክልሉ ቢላክም፤ አለመቻሉን ገልጿል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ለታህሣሥ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሳሽ መድን ድርጅት ምስክሮቹን እንዲያቀርብ በማዘዝ መዝገቡን ቀጥሮታል፡