ኢሳት ዜና:-ባለፈው ማክሰኞ ከወረዳና ከልማት ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ በቀጠለበት ሰአት የፌደራል ፖሊስ ማንኛውም ሰው በከተማው ሲንቀሳቀስ ቢገኝ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
በሺ የሚቆጠሩ የፌደራልና የክልሉ ፖሊስ አባላት በከተማው ዋና ዋና መንገዶችና ማህበራዊ አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ላይ ጥበቃ በማድረግ ህብረተሰቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስና ቤቱ ውስጥ እርፎ
እንዲቀመጥ እያስፈራሩ ነው።
በስፍራው ተገኝቶ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የደቡብ ተወካያችን እንዳለው፣ የክልሉና የፌደራል ባለስልጣናት ህዝቡ ተወካዮችን እንዲልክ ቢጠይቁም፣ ህዝቡ ግን እያንዳንዳችን የራሳችን
ተወካዮች ነን፣ ወክለን የላክናቸውንማ አስራችሁብናል በሚል እስካሁን ተወካዮችን ለመላክ ፈቃደኛ አልሆነም።
ከተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች በፈረስ ሳይቀር የተሰባሰቡት የዋካና የአካባቢው ነዋሪዎች ድርጊት ያስደነገጠው መንግስት፣ ችግሩን ለመፍታት የታሰሩትን አንዳንድ ሰዎች ለመፍታት ፈቃደኛ መሆኑን ቢገልጥም፣
ከእስረኞቹ መካከል አንዳንዶች እኛ ጥያቄያችን ሳይፈታና የታሰርንበት ምክንያት በውል ሳይነገረን ከእስር ቤት አንወጣም በማለታቸው እስካሁን አልተፈቱም።
የአካባቢው ጥያቄ ወደ ሌሎችም የክልሉ ከተሞች ሊሸጋገር ይችላል በሚል ስጋት በተለያዩ ወረዳዎች የፌደራል ፖሊስ አባላት መሰማራታቸውንም ለማወቅ ተችሎአል።
እስካሁን ድረስ ከ 30 ያላነሱ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውንና 4 ግለሰቦችም መደብደባቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ሌሎች 17 ሰዎች ደግሞ እየተፈለጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
ከተሳሩት መካከል አቶ አድነው ማሞ፣ ተፈራ ታደሰ ፣ ምትኩ በቀለ፣ ከበደ ኮኑ፣ ግርማ ጌታቸው ፣ ካሰች ተገኝ፣ አብነት አግደው፣ዘነበ ገርገራ፣ ጥረቱ ሀይሌ ይገኙበታል።
ትምህርት ቤቶች፣ ሱቆች ና ሌሎች ማህበራዊ አግልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንደተዘጉ ነው።
ችግሩ የተነሳው ከመልካም አስተዳዳር፣ ከልማትና ከአከላለል ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ የወረዳው ሊቀመንበር “በእያንዳንዳችሁ በር ላይ ድንኳን ይተከላል፣ ሞት በአየር ላይ ይረጭባችሁዋል።” ብሎ
የተናገረው።
የዞኑ ፖሊስ ደግሞ ወደ አደባባይ እወጣለሁ የምትል ወጣት እንደ 97 ሁሉ እግርህን ትቆረጣለህ ብሎ መናገሩ የህዝቡን ቁጣ ይበልጥ እንደ ጨመረው ይነገራል። ከሰአት በሁዋላ ህዝቡ ከቤቱ እንዳይወጣና ሰለማዊ ሰልፍም እንዳያደርግ በመከልከሉ ከተማው ጸጥ እንዳለ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።