በዋካ ከተማ የፌደራል ፖሊስ አሁንም ከተማውን በመቆጣጠሩ ለአራተኛ ቀን ህዝቡ እንደልቡ አንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ዘጋቢያችን ገለጠ

ኢሳት ዜና:-ባለፈው ማክሰኞ በደቡብ ክልል በዳውሮ ዞን የዋካ ከተማና አካባቢው ህዝብ ከመብት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ያነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ አንድም ሰው በመንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀስ በመከልከሉ ከተማው ጭር ብሎ መዋሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌላ፣ ተምህርትቤቶች እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች  ተናግረዋል።

በስፍራው ተገኝቶ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የደቡብ ተወካያችን እንዳለው፣ በፖሊስ ጣቢያ የነበሩት አገር ሽማግሌዎችና የህዝቡ
ተወካዮች ወደ ወህኒ ቤት እንዲላኩ ተደርጓል።

ሀሙስ እለት ህዝቡን ሰብስበው የነበሩት ባለስልጣኖች፣ ከህዝቡ ጋር ሳይግባቡ በመቅረታቸው ሁኔታውን በሀይል ለመቆጣጠር መወሰናቸው ተገልጧል።

ከማክሰኞ ጀምሮ  ከ46 በላይ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን ዘጋቢያችን ገልጧል።

ከተሳሩት መካከል አቶ አድነው ማሞ፣ ተፈራ ታደሰ ፣ ምትኩ በቀለ፣ ከበደ ኮኑ፣ ግርማ ጌታቸው ፣ ካሰች ተገኝ፣ አብነት አግደው፣ዘነበ ገርገራ፣ ጥረቱ ሀይሌ ይገኙበታል።

ችግሩ የተነሳው ከመልካም አስተዳዳር፣ ከልማትና ከወረዳ  አከላለል ጋር በተያያዘ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከብሄር ግጭት ጋር በቴአያዘ የሚነሳው ተቃውሞ እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል።