ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ግጭቱን ተከትሎ በበና ኩሌ ወረዳ አልዱባ ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ ሲወድም፣ በበና ኩሌና ሃመር ወረዳዎች አዋሳኝ በሆነው ኤሪያ አንቡሌ ቀበሌ ደግሞ የቱሪስቶች መኪና በጥይት ተመቷል።በሳላማጎ ወረዳ በኃይል-ውኃ/ ኩራዝ 2 ስኳር ፕሮጀክት ማዞሪያ በፖሊሶች ላይ በደረሰ ጥቃት ደግሞ 3 ፖሊሶች ቆስለዋል።
ግጭቶችን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር መ/ር ዓለማዬሁ መኮንን፣ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል። የአካባቢው ህዝብ ለለውጥ ዘግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጥቅምት 2/2009 ዓ.ም በበናኩሌ ወረዳ ርዕሰ መዲና -ቀይአፈር- ከተማ በደቡብ አቅጣጫ በሚገኘው አልዱባ ቀበሌ ወጣቶች ባደረጉት ተቃውሞ ፖሊስ ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ አውድመውታል።
ወጣቶቹ “ ይህ መንግስት በቃው፣ የመንግስት ለውጥ እንፈልጋለን፣ አዲስ መንግስት ይምጣልን” ማለታቸውንና ገበያውም በጊዜ መበተኑ ታውቋል። አስቀድሞ እንደተበተነ በገበያው የነበሩ እማኞች አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ቀን በበናኩሌ ወረዳና በሃመር ወረዳ አዋሳኝ የ -ኤሪያ አንቡሌ ቀበሌ በጉዞ ላይ በነበሩ ቱሪስቶች መኪና ላይ ተኩስ ተከፍቶ መስተዋቱ ተመቷል። መኪናው ላይ ከደረሰው ጉዳት በስተቀር በተጓዦች ላይ አደጋ አልደረሰም፡፡ በወረዳው ያለው ችግር ለሁለት አመታት የዘለቀ ቢሆንም እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።
ከጂንካ በምዕራብ አቅጣጫ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ወደሚገኙበት የሳላማጎ ወረዳ በሚወስደው መንገድ ወደ ኃይሎ ውሓ ወይም ኩራዝ 2 ፕሮጀክት ማዞሪያ ላይ የሀመር ወጣቶች በፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍተው- ጎርኪ፣ አይካሮ እና ሀሰን የሚባሉ ሦስት የፖሊስ አባላትን ሲቆስሉ፣ ስሙ ያልታወቀው 4ኛው ፖሊስ ህይወቱ አልፏል። ሶስቱም ጥቃቶች ግንኙነት አላቸው ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ፣ በአካባቢው የሚካሄደው ተቃውሞ እየጨመረ መምጣቱን ሲታይ፣ ጥቃቶቹና ተቃውሞዎቹ ግንኙነት እንዳላቸው ያመለክታል ብለዋል።
በርካታ አርብቶአደሮችን ያፈናቀለውና ለግጭት መንስኤ የሆነው የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ላቀረብነው ጥያቄ፣ ፕሮጀክቱ ስራ አለመጀመሩንና የአካባቢው ህዝብ ስራ ይጀምራል ብሎ እንደማያምን ገልጸዋል ።