መጋቢት ፳( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል ሰሜናዊ ዞን በሃላባ ማረቆ ወረዳ የተከሰተው መጠነ ሰፊ የርሃብ አደጋ አስከፊ መሆኑን ዩኒሴፍ አስታውቀዋል። በደቡብ ክልል ከሚገኙ 136 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ በክልሉ ትርፍ አምራች የነበሩት 73 ወረዳዎች ከፍተኛ አደጋ ይንዣበባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 45ቱ ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት አስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አመልክቶአል፡፡ ድርቁን ተከትሎ የተፈጠረው የውሃ እጥረት እንስሳት ላይም ከፍተኛ እልቂት አስከትሏል።
በማረቆ ወረዳ የዋሻ ፈቃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሰልፋ ደሎኮ ”ተማሪዎቹ በባዶ ሆዳቸው ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ። ስለሚርባቸው አትኩሮት ሰጥተው ትምህርታቸውን መከታተል ተስኗቸው በጊዜ ትምህርት አቋርጠው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።” ሲሉ ርሃቡ በማማር ማስተማሩ ሒደት ላይ አደጋ መደቀኑን አስረድተዋል።
መምህሩ ሃያ የሚሆኑ ተማሪዎች በድርቁ ሳቢያ ትምህርታቸውን አቋርጠው እቤት ለመዋል መገደዳቸውንም አስረድተዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ የ15 ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ በበኩሉ በቀበሌው አቅራቢያ ያለው የውሃ ምንጭ በመድረቁ የቤት እንስሳትን ውሃ ለማጠጣትና ለመጠጥ ውሃ ለማግኘት ሲል ረዥም መንገድ ለመጓዝ በመገደዱ ትምህርቱን አቁሞዋል፡፡
ተማሪው አክሎም፣ ትምህርት እንደሚጠቅመኝ ባውቅም ቤተሰቤን ማገዝም ግዴታዬ ነው። በዚህም ምክንያት አርፍጄ እመጣለው ወይም በጭራሽ ሳልማር እቀራለሁ ብሎአል፡፡
የደቡብ ክልል መስተዳድር ለአካባቢው አርሶ አደሮች የመጠጥ ውሃ ችግሮች ምንም ዓይነት የመፍትሔ እርምጃዎችን እስካሁን አልወሰደም።
በተመሳሳይ በአማራ፣ትግራይ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች ላይ በደረሰው ድርቅ ምክንያት ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ለማቆም ተገደዋል። በኢትዮጵያ የተከሰተውን አስከፊ የርሃብ አደጋ ጉዳተኞች ለመታደግ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ዘመቻ መጀመራቸውን ዩኒሴፍ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት እርዳታ ክፍል እንዳስታወቀው፣ አለማቀፍ እርዳታ እየቀረበ ቢሆንም፣ በወደብ መጨናነቅ ምክንያት በጅቡቲ ወደብ 80 ሺ ቶን የሚሆን ምግብ አልተራገፈም፡፡ መንግስት ለእርዳታው ቅድሚያ እንዲሰጥ ካላደረገ የሁለተኛውን ዙር ምግብ የማከፋፈል ስራ አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡