በደሴ የፌዴራል ፖሊሶች ሙስሊሞችን በቆመጥ ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ሆነ

መስከረም ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሙስሊሞቹ በፌዴራል ፖሊሶች ክፉኛ የተደበደቡት፤ <መመራት የምንፈልገው ራሳችን በመረጥነው መጂሊስ ነው!፤ መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን!>በማለት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ በማንሳታቸው ነው።

ቪዲዮውን ለኢሳት ያደረሱ አንድ የደሴ ነዋሪ<በአወሊያ ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው የሙስሊሞች መብት የማስከበር እንቅስቃሴ አንድም ጊዜ ከህጋዊና ሰላማዊ ማዕቀፍ አፈንግጦ የታየበት ጊዜ ባይኖርም፤መንግስት ግን ሲፈልግ መሪዎቻችንን ያስራል፤ሲያሻው ይደበድበናል>>ብለዋል።

<<ሌላው ቢቀር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሞቱ ጊዜ ለተወሰነ ጊዜያት ተቃውሟችንን ማቆማችን፤ ምን ያህል ህጋዊና ሰላማዊ መሆናችንን የሚያስረዳ ቢሆንም፤መንግስት ግን ይህን እውነት ላለማየት ሆን ብሎ ዐይኑን ጨፍኗል>> ብለዋል- እኚሁ የደሴ ነዋሪ።

<< ሹመኞቻችን ያዘኑ መስለው ህብረተሰቡን ለለቅሶ ውጡ እያሉ- እነሱ ግን  ውስጥ ለውስጥ ሌላ ተለጣፊ መጂሊስ ሊያስቀምጡብን ሲራወጡ መክረማቸውንም ደርሰንበታል>> ሲሉ አክለዋል።

<<ሀዘናቸውን ምንጊዜ ረስተው እኛን ወደማሳደድና ወደ መደብደብ እንደተመለሱ አልገባኝም>> ያሉት እኚሁ የድምፃችን ይሰማ ኮሚቴ አባል፤ <<እንኳን መደብደብ ቢገድሉንም ዲናችንን ጠብቀን ለመሞት ዝግጁ ነን>> ብለዋል።

የዛሬ ሁለት ወር አካባቢ በኔዘርላንድ-ሮተርዳም በመደበኛ ሥራቸው ላይ ተሰማርተው የነበሩ አንድ ወንድና አንድ ሴት ፖሊሶችን- አልኮል ጠጥቶ የሰከረ ሰው ይሰድባቸዋል።

በተለይ  ጠጪው ግለሰቡ ሴቷን ፖሊስ፤ ኤጀንት ስኮፕትን ጸያፍ የብልግና ቃል በማውጣት ይዘልፋታል።

ስድቡ ሲደጋገምባት ንዴቷን መቆጣጠር የተሳናት ኤጀንት ስኮፕትም፤ ሰውዬውን በጫማ ጥፊ ደጋግማ በመምታት ከባልደረባዋ ጋር የፊጥኝ ታስረዋለች።

ይህን ድርጊት ከርቀት ሆኖ ይከታተል የነበረ አንድ መንገደኛ በሞባይል ቴሌፎኑ በመቅረጽ ለሚዲያ ይሰጠዋል። በኔዘርላንድ የሚገኙ  እጅግ  በርካታ ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ወሬውን ከምስሉ ጋር አናኙት።ክስተቱ ፤ከዳር እስከ ዳር የአገሬው መነጋገሪያ ሆነ።

ስኮፕት በጠጣው ሰው ላይ የወሰደችው እርምጃ ፤ኔዘርላንዳውያንን ብቻ ሳይሆን መንግስታቸውን ጭምር አስቆጣ።

ፖሊሶች፣የህግ ባለሙያዎች፣የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣የፓርላማ አባላትና ሌሎች ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየሬዲዮው እና በየቴሌቪዥኑ እየቀረቡ በፖሊስ ስኮፕት ድርጊት ቁጣቸውን ገለጹ።በኔዘርላንድ ፖሊስ  ፈጽሞ የዚያ ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም  ስለማይታይ ብቻ ሳይሆን-  ይፈጸማል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው  የስኮፕት ድርጊት እንደ አዲስ ነገር አገሩን ጫፍ እስከ ጫፍ <ጉድ> ያሰኘው።

የአባሉን ድርጊት አጥብቆ የኮነነው ራሱ የኔዘርላንድ ፖሊስ፤ ኤጄንት ስኮፕት ፈጽመዋለች ባለው ጥፋት ላይ ምርመራ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በምርመራው ፍፃሜ ከሥራ እስከመወገድ የሚደርስ ጠንካራ ቅጣት እንደሚጠብቃት ከወዲሁ አስተያቶች ይሰማሉ።

<<ኢትኦጵያ ውስጥ ዜጎች ብዙ ጊዜ የሚታሰሩትና የሚደበደቡት ፖሊሶችን ስለሰደቡ ሳይሆን የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው>>ያሉ  ዜናውን የተከታተሉ  በሮተርዳም የሚኖሩ አንድ  ኢትዮጵያዊ፤<<በዚያ ላይ እኛ ጋር  ድብደባው በመንግስት ትዕዛዝና ድጋፍ የሚፈፀም መሆኑ፤ የኢትዮጵያውያን የሰውነት ክብር -ከሌሎች  ጋር ሲነፃጸር ምን ያህል የወደቀበትና  ከእንስሳ የማይሻልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ አመላካች ነው>ሲሉ ተናግረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide