(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2010)
በደሴ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ተሰማ።
ፒያሳ በሚባለው አካባቢ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የደረሰውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ የእስር ርምጃ በመወሰድ ላይ መሆኑም ታውቋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የትግል ጥሪ ወረቀት ሲበተን አድሯል።
በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በተበተነው በዚሁ የትግል ጥሪ ህዝቡ የህወሃትን አገዛዝ ለማስወገድ እንዲነሳ ተጠይቋል።
ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አልተቻለም።
የቦምቡ ጥቃት ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የቦምቡ ጥቃት የተፈጸመው በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
ቦምቡ ከመፈንዳቱ በፊት በአካባቢው መብራት እንዲቋረጥ መደረጉ ጥቃቱ የተቀነባበረ ለመሆኑ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
በወቅቱ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ፍንዳታውንና ተኩስን ተከትሎም በደሴ ከተማ ወጣቶችን የማፈስ ዘመቻ መካሄዱን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ‘’አርበኞች ግንቦት ሰባት’’ ከተማ ውስጥ ሰርጎ ስለገባ አሰሳ እያደረግን ነው የሚል ሽፋን መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ለጊዜው ቁጥራቸው ባይታወቅም በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከቅዳሜው የቦምብ ጥቃት በኋላ ደሴ በውጥረት ውስጥ ስትሆን ተጨማሪ የአገዛዙ ወታደሮችም ወደ ከተማዋ መግባታቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል ትላንት ሌሊቱን በአዲስ አበባ ከተማ የትግል ጥሪ ወረቀት ሲበተን ማደሩን ለማወቅ ተችሏል።
ቢቢኤን በላከልን መረጃ ላይ እንደተመለከተው የአዲስ አበባ ወጣቶች ያዘጋጁት የጥሪ ወረቀት በከተማዋ በተለያዩ መንደሮች በስፋት ተሰራጭቷል።
በማሰር በመግደል የሙስሊሙን ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አሁንም ለረጅም ትግል ተዘጋጅተናል፣ የትግል መርሃችንና አንድነታችን ምንጊዜም የማንነታችን ጽኑ መሰረቶቻችን ናቸው፣ ግዙፍ ህዝባዊ ንቅናቄያችን በሃይል ርምጃ አይገታም፣ የአንድ ብሄር የበላይነት ያለባት ሃገር ማየት አንፈልግም፣ ድፍን ሀገር እስር ቤት ሆና እያለ እስር ቤቶች ዘግተናል ማለት ፌዝ ነው፣ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ ዘረኝነት ይውደም፣ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች በበራሪ ወረቀት ተዘጋጅተው እንደተሰራጩ በፎቶግራፍ ተደግፎ ከመጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።