የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሀገር መክዳትና በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2010)

ፋይል

የሰራዊቱን አባላት ለማስከዳትና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጎን እንዲሰለፉ ሲቀሰቅሱ ነበር የተባሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሀገር መክዳትና የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው።

ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ይፈታሉ የሚል መግለጫ በተሰጠ ማግስት ክስ የተመሰረተባቸው እነዚህ ወታደሮች 5 መሆናቸውም ታውቋል።

ሕገመንግስታዊውን ስርአት ለመጠበቅ የተሰጣቸውን አደራ በመተው የኦነግን የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፣ሌሎች የሰራዊት አባላትንም ሲመለምሉ ነበር በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው።

ተከሳሾቹ ምክትል የአስር አለቃ እስክንድር አደም፣የአስር አለቃ ሽመልስ ብርሃኑ፣ ወታደር ኢብራሂም ጉሬ፣ወታደር ኢብራሂም ጫላ ኢማናና ወታደር ሃብታሙ ፋና የተባሉ የሰራዊቱ አባላት መሆናቸው ተመልክቷል።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ምዕራብ ዕዝ ሰራዊት አባላት መሆናቸው የተጠቀሰው ተከሳሾች ሁሉም ነዋሪነታቸው በሶማሌ ክልል ቆራሔ ደብረወይኒ መሆኑም በክሱ ውስጥ ተገልጿል።

“ኦነግን እንቀላቀል” በማለት የታጠቁትን የጦር መሳሪያ እንደያዙ በቅስቀሳና በምልመላ ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር በሚል ክስ የተመሰረተባቸው አምስቱ የሰራዊቱ አባላት ከሰራዊቱ ባሻገር በሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ውስጥ ምልመላ ሲካሄድ እንደነበር ተገልጿል።

በሶማሌ ክልል ልዩ ስሙ ካሉብ ነዳጅ ማውጪያ አካባቢ በነበሩ የሰራዊቱ አባላት ላይ በዋናነት የምልመላ ስራ ማካሄዳቸውንም አቃቤ ህግን ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

ተከሳሾቹ በሀገር መክዳትና በአሸባሪነት ክስ እንደተመሰረተባቸውም ታውቋል።

መንግስት እስረኞቹን ለመፍታት ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በይፋ ይሰረዛሉ ተብለው ከሚጠበቁት አዋጆች አንዱ የጸረ ሽብር አዋጁ ቢሆንም መንግስት ይህን አዋጅ በመጠቀም ክሱን መቀጠሉ አነጋጋሪ ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በግንቦት 7 ተጠርጥረው ከታሰሩት እስረኞች ውስጥ ግሩም አስናቀው የተባለ ተከሳሽ የአራት አመት የእስር ውሳኔ እንደተላለፈበት ታውቋል።

የአራት አመታት እስራት የተፈረደበት ግሩም አስናቀው በእነ ትንሳኤ በሪሶ የክስ መዝገብ ላይ ከተከሰሱት ውስጥ በተራ ቁጥር 3 ላይ የተመዘገበ መሆኑም ተመልክቷል።

ተከሳሹ የቀረበበት ብቸኛ ሰነድ የስልክ የጽሁፍ ማስረጃ ሲሆን የተጠቀሰው የጽሁፍ ማስረጃ የእሱ እንዳልሆነና ተገኘ የተባለው መረጃም ከሱ ስልክ እንዳልተገኘም መከራከሩ ተመልክቷል።

የኢሕአዴስ ስራ አስፈጻሚ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩ እስረኞችን ለመፍታት ውሳኔ ባሳለፈ ማግስት ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ክሶች መቀጠላቸውና ፍርድ እየተሰጠ መገኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል።