በደሴ ከተማ ሙስሊሞች ከፌደራል ፖሊስ ጋር ተጋጩ

ነሀሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጁመኣን ሶላት ጸሎት ለማድረስ ዛሬ በደሴ አረብገንዳ የተሰባሰቡ ሙስሊሞች ከፖሊስ ጋር ሲጋጩ ውለዋል።

በደሴና አካባቢዋ የሚገኙ ሙስሊሞች አረብገንዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው መስጊድ ለመስገድ በሚሰባሰቡበት ወቅት፣ በስፍራው ሲጠባበቁ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በመስጊዱ ጸሎት ማድረስ አይቻልም በማለት መከልከላቸውን ተከትሎ ነው ችግሩ የተፈጠረው።

ፖሊሶቹ ” ሁላችሁም በአካባቢያችሁ በሚገኙ መስጊዶች መስገድ ትችላላችሁ፣ ወደ ዚህ ቦታ የምትመጡት ግን ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ነው በማለት” ሲያስታዉቁ፣ ሙስሊሞች በበኩላቸው ” ብላችሁ ብላችሁ የምንሰግድበትን መስጊድ እናንተው ትመርጡልን ጀመር” በማለት ውዝግቡ ተጀምሯል።

ፖሊሶቹ በምእመኑ ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀምሩ፣ ምእመኑም በፖሊሶች ላይ ድንጋይ በመወርወር የአጸፋ እርምጃ ወስዳል።

በዚሁ ውዝግብ ከ5 ያላነሱ ፖሊሶች ሲቆስሉ ከምእመኑ ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ ለማወቅ አልተቻለም። ይሁን እንጅ በርካታ ወጣቶች በፖሊስ መኪኖች ተጭነው ተወስደወዋል፣ ጉዳት የደረሰባቸውም በርካታ መሆናቸው ታውቋል።

ዘገባውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ፖሊሶች መንገዶችን በማጠር በአካባቢው የሚዘዋወረውን ሙስሊም ሁሉ እየያዙ በማሰር ላይ ናቸው።

በርካታ የንግድ ድርጅቶች የተዘጉ ሲሆን፣ በከተማውም ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

በአዲስ አበባም ቁጥሩ ከ 500 ሺ እስከ 800 ሺ የሚጠጋ ህዝብ ዛሬ በአንዋር መስኪድ ተካሂዷል። መሪዎቹ እንዲፈቱም በድምጽ ጠይቋል።

በጅማ ፣ በሻሸመኔ ሶስት መሲኪዶች  እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጓል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ወርቅነህ ገበየሁ ከሁለት ቀናት በፊት ፦ “ህብረተሰቡ ተረባርቦ ይሄንን ተቃውሞ የማያስቆም ከሆነ፤ የከፋ ነገር ይመጣል!” በማለት ማስጠንቀቃቸውን ይታወሳል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide