ህዳር ፰ (ሰምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በአንድ አርሶአደርና ባለቤታቸው ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይፋ ካደረገ በሁዋላ ኢትዮጵያውያንን ከያቅጣጫው እያስቆጣ መሆኑን ኢሳት ያነጋገራቸው እንዲሁም ለኢሳት መልእክቶችን የሚተው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ አንድ አስተያየት ሰጪ በድርጊቱ ማዘን ብቻውን በቂ አለመሆኑን ገልጸው ወደ ተግባር መግባት አለብን ሲሉ አሳስበዋል። ሌላው በዳላስ ቴክሳስ የሚኖሩ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ ውርደት እንደሌለ ገልጸዋል ።
በውጭ አገር የሚኖረው ሌላው ኢትዮጵያዊ በበኩሉ በአንድነት እስካልቆምን ድረስ ኢህአዴግ ተመሳሳይ የሆነ ግፍ እየፈጸመ ይቀጥላል ብሎአል)
ስንታየሁ ጸጋየ የተባለች ኢትዮጵያዊትም በሰው አገር ላይ ያልተፈጸመብን ድርጊት በአገራችን ላይ ተፈጽሞ ስናየው በምን ደረጃ ላይ እንገኛለን ብየ እንድንጠይቅ አድርጎኛል ብላለች።
በድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ፖሊሶች አለመያዛቸውን በመግለጽ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሶሎሞን መኮንን፣ በድርጊቱ የተሳተፈ ፖሊስ አለመኖሩንና ፖሊሶች ተሳትፈዋል በማለት የሚያስወሩት የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማራመድ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በሴትዮዋ ላይ የተፈጸመ ችግር ቢኖርም በአንዳንድ ሁኔታዎች ለፖለቲካ አላማ ተብሎ ተጋኖ የቀረበበት ሁኔታ አለ ብለዋል
ባለስልጣኑ ጉዳዩ በወረዳ ደረጃ የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው አፋጣኝ ፍርድ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።
የኢህአዴግ አባላት የሆኑት የገብሮ ቀበሌ ሊቀመንበር እንዲሁም የምክር ቤት አባላት ኢሰብአዊ ድርጊት መፈጸሙን በድምጽ መናገራቸው ይታወቃል።
ኢሳት ባደረገው ማጣራት ጉዳት የደረሰባት ወጣት ሴት አርሶአደር አሁንም በህክም ላይ ናት።