ሰኔ አስራ አራት ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ከፌደራል ፖሊስ የኢሳት ምንጮች በተገኘው መረጃ የፍርድ ቤቶችን መዘጋት አስታኮ በክረምቱ ወራት ከአንድነት ፓርቲ፣ ከፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እና ከፍትህ ጋዜጣ የሚታሰሩ መንግስት ስጋቴ ናቸው ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ። እንደመረጃ ምንጮች ሰዎችን በክረምት ለማሰር የተፈለገው ግለሰቦችን በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ለማሰቃየት እንዲያመች ነው። እስካሁን ድረስ እነማን ይታሰሩ እንማን ይቅሩ በሚለው ላይ የፖለቲካ ውሳኔ አልተሰጠም፣ ይሁን እንጅ ለእነዚህ ሰዎች ማሰሪያ ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ በከፍተኛ የደህንነት ከበባ ውስጥ እንደሚገኝ ለአዘጋጁ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ተናገሩ። በመኖሪያ ቤቱ ፣ በስራ ቦታው እንዲሁም በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ የሚከተሉት የደህንነት ሀይሎች አሉ። በግል ስልኩ፣ በመስሪያ ቤት ስልኩ፣ በኢሜሉ የማያውቃቸው ባእድ መልክቶች እየደረሱት ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች ከሶስት ሳምንት በፊት ጀምሮ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ቅሊንቶ መውረዳቸው ታውቋል። ቅሊንቶ እስር ቤት የሚገኘው ቃሊቲ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ራቅ ብሎ የሚገኝ፣ መንገዱ በጋሪ ካልሆነ በመኪና የማይኬድበት ነው። አዲሱ እስር ቤት መጀመሪያ ለትምህርት ቤት የተሰራ ቢሆንም፣ እስረኛ በመብዛቱ እና በቅርቡም ብዙ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ስለሚታሰሩ ወደ እስር ቤትነት መቀየሩን ዘጋቢያችን ገልጧል።
ከዚሁ ከእስር ቤት ዜና ሳንወጣ ጋዜጠኛ እና መምህርት ርእዮት አለሙ ከታሰረች ዛሬ አንድ አመት ሞልቷታል። የቃሊቲ ምንጮች እንደገለጡት የታሰረችበትን አንደኛ አመት ሻማ በመለኮስ አክብራለች። ነገ ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓም ርእዮት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ክርክሩዋን ትጀምራለች።
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide