በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ውስጥ አንዱን ብሔር ማግለልና ሌላውን ማወደስ ይታያል ተባለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 29/2010)

በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ውስጥ አንዱን ብሔር ማግለልና ሌላውን ማወደስ እንደሚታይ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የቀድሞ ተማሪዎች የሚሰባሰቡት በፖለቲካና በርዕዮተ አለም አመለከታተቸው ነበር ብለዋል።

በአፋር ክልል የሕወሃት አገዛዝ ኣያከበረ ያለውን “የብሔረሰቦች ቀን” በማስመልከት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ እየተየ ያለውን ተቃውሞና አመጽ በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ሃይለማርያም በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ ብሄር ተኮር በሆነ መልኩ አንዱን ብሔር የማግለልና ሌላውን ማወደስ ይታያል ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።

ይሄ ኋላቀር የሆነ አመለካከት በመሆኑ መቀረፍ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

የድሮ ተማሪዎች በአንድ ልብ የሚሰባሰቡት በፖለቲካ አመለካከትና ርዕዩተ አለም ነው ብለዋል።

በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የቀድሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤል መንግስት በፖሊሲ ደረጃ የብሔር አደረጃጀት በዩኒቨርቲ ውስጥ እንዲተገበር ካደረገ በኋላ ተማሪዎችን ተጠያቂ ማድረጉ ስህተት ነው ብለዋል።

በአርባምንጭም ሆነ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የትግራይ ተወላጆችን በሕወሃት፣የኦሮሞ ተወላጆችን በኦህዴድ፣የአማራ ተወላጆችን በብአዴን የሚያደራጅ መዋቅር ተዘርግቶ የሚሰራበት ሁኔታ አለ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተማሪዎች በፖለቲካ አመለካከታቸውና ርዕዮተአለም የሚሰባሰቡበት እድል የለም ብለዋል ።

አቶ እንዳልካቸው ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉ ይህ የአቶ ሃይለማርያም ንግግር ሕወሃት/ኢህአዴግ የሚመራበት የብሄር ፖለቲካ መክሸፉን አመላካች ነው ብለዋል።