በዝናብ እጥረት የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

ኢሳት ዜና (ነሐሴ 19 2997)

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ተከስቶ ያለው ድርቅ የምግብ ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ  እንዲሄድ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት የተጨማሪ የ230 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጥሪ ማቅረቡን ሮይተርስ ዘግቧል ።

ለምግብ እጥረት አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱ 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑት በተያዘው አመት አስቸኳይ የምግብ እርዳታን እንደሚፈልጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

በሀገሪቱ የተከሰተው የዝናብ እጥረት አደጋ ከተተነበየው የከፋ ነው ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ሀላፊዎች በምግብ እጥረቱ የሚጎዱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ይፋ አድርጓል ።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅርት የእርዳታ ማስተባበሪያ ተወካይ የሆኑት ዴቪድ ዴል-ኮንቴ በተለያዩ ክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ እስከ ሚያዚያ ወር 2008 አ.ም ቀጣይ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ።

በአፋር ክልል በርካታ እንስሦችን የገደለው የድርቅ አደጋ በአማራ ከልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ተመሳሳይ ጉዳት ማድረስ መጀመሩን ነዋሪዎች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

በበልግ ወቅት ያጋጠመው የዘናብ እጥረት በመደበኛው በክረምት ወቅትም በመደገሙ ምክኒያት ችግሩ የከፋ ሊሆን መቻሉን በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ድርጅት ተውካይ የሆኑት ጆን አይሌፍ ለሮይተርስ አስረድተዋል።

የተለያዩ አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያጋጠመው ድርቅ በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የቅርብ ከትትል እንደሚፈልግ በማሳሰብ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሀገሪቱ ያጋጠመውን የምግብ እጥረት ተከትሎ መንግስት ያለ ጨረታ የስንዴ ግዢን ከውጪ ለማስገባት መወሰኑን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

የስንዴ አቅርቦቱ አጣዳፊ በመሆን ምክኒያት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ስንዴው ያለ ጨረታ ተገብቶ በአስቸኳይ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መወሰኑ ታውቋል።

ለኢትዮጵያ መንግስት ስንዴ በማቅረብ ከሚታወቁት 40 ኩባንያዎች መካከል ሰባቱ ስንዴውን እንዲያቀርብ ጥያቄ መቅረቡን የድርጅቱ ሀላፊዎች አስረድተዋል።

ይሁንና ሀላፊዎቹ የተመረጡትን ስንዴ አቅራቢዎች ኩባንያ ስም ዝርዝር ይፋ ከማድረግ የተቆጠቡ ሲሆን ስንዴውንም በቀጣዩ ጥቂት ወራቶች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እቅድ መያዙን ለመረዳት ተችሏል።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ 222 ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴን ከውጪ ለማስገባት መወሰኑን ይታወሳል ።

በተያዘው የክረምት ወር ያጋጠመውን የዝናብ እጥረት ተከትሎም በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የምግብ ዋጋ በመጨመር ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።