ጥር 24 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ላለፉት አራት ወራት በዋካ ከተፈጠረው ረብሻ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩት ወጣቶች በገደብ ተፈቱ፣ ወጣቶችን በግንቦት 7 ስም ለመክሰስ ተዘጋጅቶ የነበረው ክስ በወጣቶቹ ጥንካሬ እንዲከሽፍ ተደርጓል።
ለነጻነት ሰመአቱ የኔሰው ገብሬ ህልፈት ምክንያት የሆነው ፣ የዋካ ወጣቶች እስር የመንግስትን የፍትህ ስርአት ያጋለጠ እንደነበር የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
በዋካ ከወረዳ እና ከመብት ጥያቄዎች ጋር በተነሳ ረብሻ በርካታ ወጣቶች ታስረው በመጨረሻ 7 ወጣቶች ማለትም ፣ ቻላቸው ሀይለማርያም፣ ካሳሁን ባቲሳ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ አስራት ጊነቶ፣ ጥራቱ ወልደማርያም፣ ግርማ ማሞና ቶምቦ ውጁ ፣ረብሻውን የመራችሁና ያስተባበራችሁ እናንተ ናችሁ ተብለው ላለፉት አራት ወራት በእስር እንዲማቅቁ ተደርጓል።
የዞኑ አቃቢ ህግ የወጠቶችን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ፣ ወጣቶች በሽብርተኝነት እንዲከሰሱ ጥያቄ አቅርቦባቸዋል።
አቃቢ ህግ ባቀረበው ክስ ወጣቶቹ በውጭ አገር ከሚገኙ የግንቦት7 ፣ የኢሳት ጋዜጠኛ እና በስዊድን ኗሪ ከሆነው የዋካ ተወላጁ ከአቶ ፍሰሀ ተሰማ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎአል።
በዋካ ለተፈጠረው ረብሻም የግንቦት7 እጅ አለበት ሲል አቃቢ ህጉ ክሱን አዘጋጅቶ አቅርቧል። ይሁን እንጅ የፌደራል መንግስቱ ፣ ወጣቶችን በሽብርተኝነት ለመክሰስ እና ረብሻውን ከግንቦት7 ጋር ማያያዝ፣ የመንግስትን ምስል የሚያበላሽ በመሆኑ ክሱ በሌላ መንገድ እንዲዘጋጅ መመሪያ ሰጥቷል።
የዞኑ ባለስልጣናት ክሱን ባቀረቡበት ወቅት ወጣት እስረኞቹን ከኢሳት ጋዜጠኛ እና ከመምህር ፍሰሀን ጋር ተገናኝተናል ብላችሁ ፈርሞ ሲባሉ፣ እኛ ጋዜጠኛውንም መምህር ፍሰሀንም አናውቃቸውም፣ ምንም የምንፈርመውም ጉዳይ የለም በሚል መልስ ሰጥተዋል።
በወጣቶቹ እንቢተኝነት የተበሳጩት የዞኑ ባለስልጣናት፣ እኛ እናንተን አንፈልጋችሁም፣ የምንፈልጋቸው የኢሳትን ጋዜጠኛ እና መመህሩን ነው፣ እናንተ ለምን ዝም ብላችሁ ፈርማችሁ አትወጡም ተብሎ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሎአል።
የአካባቢው ህዝብ በወጣቶች መታሰር ተቃውሞውን በተለያዩ መንገዶች መግለጡ፣ ተጨማሪ ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ሰበብ ከትናንት በስቲያ በሶስት አመት የጊዜ ገደብ ወጣቶች እንዲለቀቁ ተድረጓል።
ኢሳት ከተወሰኑ እስረኞች ጋር ባደረገው ውይይት ከፍተኛ የሆነ እንግልት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ችሎአል።
“ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጭንቅት እንዲደርስብን አድርገዋል፤ ግፍ ፈጽመውብናል ሁኔታውን ስንረጋጋ እናጋልጣለን” በማለት ተናግሯል። ወጣቶቹ በሶስት አመታት ውስጥ አንድ ችግር ፈጥረው ቢገኙ በሽብርተኝነት ክስ እንደሚመሰረትባቸው እንደተነገራቸው ገልጠዋል።
የአካባቢው ሽማግሌዎች በወጣቶቹ ላይ ገደብ ጥሎ መፍታቱ ተገቢ አይደለም በሚል አቤቱታ ለማቅረብ እየተዘጋጁ ነው።በዋካ እና አካባቢዋ አሁንም ድረስ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሰፍረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።
መምህር የየኔሰው ገብሬ ራሱን በእሳት አጋይቶ ከገደለ በሁዋላ ዋካ የአለምን የመገናኛ ትኩረት መሳቡዋ ይታወሳል።