በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከ7 በላይ ተማሪዎች መጎዳታቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2010)

በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በተከሰተ ግጭት ከ7 በላይ ተማሪዎች ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ።

ግጭቱ ብሔርን መሰረት አድርጎ መቀስቀሱን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ዩኒቨርስቲው ግጭቱን ለማርገብና ለመቆጣጠር ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙ ታውቋል።

በሆሳዕና ከተማ ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ብሔርን መሰረት ያደረገ ግጭት በመፈጠሩ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እስከመውጣት ደርሰዋል።

የችግሩ መንስኤ በሁለት ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የተነሳ ነው ቢባልም ቀደም ብሎም ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንደነበሩ ነው የተገለጸው።

በተለይ ከ1 ሺ የሚበልጡ የኦሮሚያ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን የዩኒቨርስቲው አመራሮች ገልጸዋል።

በዩኒቨርስቲው በተከሰተው ግጭት በሰባት ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሶ ሆስፒታል መግባታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በተለይም በ3 ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው የተባለው።

ከፍተኛ ጉዳቱ የደረሰውም በ2 የኦሮሞና አንድ የደቡብ ተማሪዎች ላይ መሆኑን የዩኒቨርስቲው አመራሮች ገልጸዋል።

ከ18ሺ በላይ መደበኛና ተከታታይ ተማሪዎችን በያዘው የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድ የዞኑ አስተዳዳሪዎችና የዩኒቨርስቲው አመራሮች ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ተብሏል።

ተማሪዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ግን እንደተቸገሩ ነው የተገለጸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ተማሪዎች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ከ32 ዩኒቨርስቲዎችም በ26ቱ ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን የሪፖርተር ዘገባ አስታውሷል።