(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2011)በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መደበቅና እንዳይያዙ ከለላ መስጠት በአሰራሩ ላይ ችግር እየፈጠረበት መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ገለጸ።
ወንጀሎችን ከተደበቁበት ለማውጣትና ለህግ ለማቅረብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ እንዲሰጥ ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ጠይቀዋል።
የተወካዮች ምክርቤት የጠቅላይ አቃቤህግ የ5 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሌብነት የተጠረጠሩ ሰዎችን በመያዝ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በርካታ ርምጃዎች ተወስደዋል።
በተለይም ከፍተኛ የሃገር ሃብት የዘረፉና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ባለስልጣናትን ጨምሮ ብዙዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ያስታወሱት።
ይህም ሆኖ ግን አሁንም ያልተያዙ ቀንደኛ ወንጀለኞች እንዳሉ አቃቤ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ አልሸሸጉም።
እንደ ዋና አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ገለጻ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መደበቅና እንዳይያዙ ከለላ የሚሰጡ መንግስታዊ አካላት አሉ።
እናም ይህ ችግር በፍትህ ስርዓቱ ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ነው የገለጹት።
ስለሆነም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በእነዚሁ አካላት ላይ አቋም በመውሰድ ለአቃቤ ህግ ድጋፍ እንዲሰጥ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ጠይቀዋል።
በአቃቤ ህግ ከሚፈልጉትና የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ዋነኛ ተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ አንዱ ናቸው።
አቶ ጌታቸው አሰፋ በመቀሌ መሽገው በህወሃት በኩል ከለላ እንደተሰጣቸው ይታወቃል።
ይህም የሆነበት ምክንያት ዋና አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እንደገለጹት ወንጀልንና ፖለቲካን ባለመለያየት ሁለቱንም ሁኔታዎች የመደባለቅ አዝማሚያ በመኖሩ ነው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ፖለቲካና ወንጀል የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እናም አቃቤ ህግ በፖለቲካ ሳይሆን ወንጀለኞችን ለይቶ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።