ታህሳስ 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እንደ ጋዜጣው ዘገባ ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ልዩ ቦታው ቀበሌ 014 በሚባለው የድንበር ቀበሌ ውስጥ በወሎየዎችና በአፋሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ ሰው ሲሞት፤ 45 ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን፤በርካታ ከብቶችና ግመሎች መሞታቸውና ንብረቶች መውደማቸውም ተመልክቷል፡፡
ይሁንና የሞተው አንድ ሰው ከየት ወገን እንደሆነና የተቃጠሉት ቤቶችም የነ ማን እንደሆኑ ጋዜጣው በዝርዝር የገለጸው ነገር የለም።
ስለተፈጠረው ግጭት በጋዜጠኖች የተጠየቁት የወረዳው ፀጥታ ኃላፊ፦” ጉዳዩ በባለሙያዎች እየተገመገመ ነው” ብለዋል፡፡
በአካባቢው በሚኖሩ አማራዎችና አፋሮች መካከል በግጦሽ ሳር ምክንያት የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት የጐሳ መሪዎች “ጥረት እያደረግን ነው” ቢሉም ፤ምንም ውጤት አለመገኘቱን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የመስተዳድሩ ሃላፊዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም” ሲሉ አስተዳዳሪዎቻቸውን ይከሳሉ፡፡
የወረዳው አስተዳደር ፀጥታ ኃላፊ አቶ መኮንን ሁሴን ደመኔ ፦ “ከፌደራልና ከተለያዩ ቦታዎች በተሰባሰቡ ባለሙያዎች ጉዳዩ ግጭት ነው? ወይስ ወንጀል? የሚለውን ለማየትና ግምገማ ለማድረግ ለዛሬ ፕሮግራም ይዘናል፡፡ ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ ከምሰጥ፤ ከግምገማው በኋላ የተሟላ መረጃ ይሻላል” በማለታቸው፤ጋዜጣው ወደ ህትመት እስከገባበት ሰዓት ድረስ የግምገማውን ውጤት ማካተት እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡