በኮንሶ የታሰሩ 52 ሰላማዊ ሰዎች አልተፈቱም ጋዜጣ አንብባችኋል የተባሉ ስድስት ሰዎች ታሰሩ
(ኢሳት ዜና የካቲት 9 ቀን 2010ዓ/ም) በኮንሶ የማንነት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት መብታቸውን የተየቁ የአካባቢው ተወላጆች በጅምላ መታሰራቸው ይታወሳል። በወቅቱ በተነሳው ግጭት ምክንያት አመጽ አነሳስታችኋል ተብለው በጅምላ ከታሰሩት ውስጥ 52 ሰላማዊ ሰልፈኞች በምህረት አዋጁ ይፈታሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተፈቱም።
በጂንካ፣ ጉዶሌ፣ ደራሼና በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ታስረው የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙባቸው መሆኑም ታውቋል። እስረኞቹ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እስረኞች ያገኙትን በምህረት የመለቀቅ መብት ተነፍገው በእስር ቤት እንዲቆዩ ለምን እንደተደረገ ማወቅ ባለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው የጉዳተኞቹ ቤተሰቦች ይናገራሉ። በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት አገዛዝ አለ ወይ? ሲሉ ውሳኔውን ኮንነዋል።
በተጨማሪም በቅርቡ ተቃዋሚ የሆነውን የሰማያዊ ፓርቲ ጋዜጣ አንብባችኋል የተባሉ ስድስት ግለሰቦች በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል። በወቅቱ በተከሰተው የኮንሶው ግጭት በአገዛዙ የጸጥታ ኃይሎች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ብዛት ያላቸው መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸው ይታወሳል። ይህን ዓይነት የጭካኔ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ትእዛዝ የሰጡ የክልሉ ባለስልጣናትም ሆኑ እርምጃውን የወሰዱ ታጣቂዎች እስካሁን በሕግ ተጠያቂ አልሆኑም።
በተጨማሪም በትናንተናው እለት በመተሃራ አዲስ ከተማ በሳምንታዊው ሃሙስ ገበያ ማእከል ግጭት ተቀስቅሶ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ምንጮች ገልጸዋል።