የ19 አመቱ ወጣት በ17 የተለያዩ ወንጀሎች ይጠየቃል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 9/2010)

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት በአንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 17 ተማሪዎችን የገደለው የ19 አመቱ ወጣት በ17 የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚጠየቅ ተገለጸ።

በማርጆሪ ስቶን ማን ዳግላስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተኩስ በመክፈት ግድያ የፈጸመው ወጣት ኒኮላስ ጃኮብ ክሩዝ የ49 አመቱን የትምህርት ቤቱን የአትሌቲክስ ዳይሬክተር ጨምሮ እድሜያቸው ከ15 እስከ 18 አመት የሆኑ ተማሪዎችን ገድሏል።

በሀገሬው አቆጣጠር እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት 14/2018 ከሰአት 2 ሰአት ከ20 ፒ ኤም ሲል በኡበር ታክሲ ማርጆሪ ስቶን ማን ዳግላስ ትምህርት ቤት ደጃፍ መድረሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የ19 አመቱ ነፍሰ ገዳይ ኒኮላስ ጃኮብ ክሩዝ የተማሪዎች መውጫ ሰአት በመቃረቡም የመግቢያ በሮች መከፋፈታቸውን ተከትሎ የትምህርት ቤቱን ካኒቴራ ለብሶ ወደ ውስጥ ገብቷል ሲል ያክላል ዘገባው።

ወደ ውስጥ ከገባ በኋላም በቦርሳ ተሽክሞት የገባውን መሳሪያ በ2ኛ ፎቅ መታጠቢያ ክፍል ከገጣጠመ በኋላ ወደ ግድያ መሰማራቱን ዩ ኤስ ቱደይ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

ግድያውን ከፈጸመ በኋላም መሳሪያውን ፈቶ ወደ ሻንጣው በመመለስና ከተማሪዎች ጋር በመቀላቀል አምልጧል።

በአካባቢው ባለ ማክዶናልድ ምግብ ቤት ለ30 ደቂቃ ያህል ቆይታ ካደረገ በኋላ ቢሰውርም ፖሊስ በ40 ደቂቃ ውስጥ ተከትሎ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

17 ሰዎችን በገደለ ማግስት 17 ክሶች የተመሰረቱበት የ19 አመቱ ነፍሰ ገዳይ ኒኮላስ ጃኮብ ክሩዝ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዳያገኝ ከልክሎት በወህኒ ይገኛል።

በፍሎሪዳ ግዛት ፓርክላንድ በሚገኘው ማርጆሪ ስቶን ማን ዳግላስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈጸመው ግድያ የ49 አመቱን የትምህርት ቤቱ የአትሌቲክስ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ሂክሰንና የትምህርት ቤቱን የፉትቦል ምክትል አሰልጣኝ የ37 አመቱን ኦሮን ፊስን ጨምሮ በአጠቃላይ 17 ሰዎች ተገድለዋል።

በዚህ አስደንጋጭ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት 15ቱ ተማሪዎች እድሜ ከ15 እስከ 18 አመት መሆኑም ታውቋል።