“በክልላችን ባለፉት ሁለትና ሶስት ወራት ብቻ ለውጡን የማይመጥኑ አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባራት እየተከሰቱ ስለሆነ ፣ለውጡ እንዳይቀለበስ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል”ሲሉ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሣሰቡ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 07 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ህገወጥ ድርጊቶችን አስመልክተው በፌስቡክ ገጻቸው በተለይ ለክልሉ ለውጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ፣ባለፉት ሁለት እና ሦስት አመታት ተኪ የሌለውን ህይወታችሁን ጭምር ከፍላችሁ ዛሬ የነፃነት፣ የፍትህ እና የእኩልነት ድባብ እንድንጎናጸፍ፤ እንዲሁም የአንድነት፣ የመከባበር ፣ የፍቅር እና የይቅር ባይነት መንፈስ እና ተስፋእንዲለመልም አስችላችኋል በማለት አወድሰዋል።
ትግላችሁ፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ጭቆና ቦታቸውን ለፍቅር፣ ለይቅርባይነትና ለነፃነት እንዲለቁ በማድረግ ማንም ባልገመተው ፍጥነትበለውጥ ተስፋ እንድንሞላ አድርጎናል ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
“አሁን የምንገኝበት ወቅት ለውጡ ከተስፋ ተራምዶ የኋላ ማርሽ በማያስገባበት ደረጃ ላይ አልደረሰም” ያሉት አቶ ንጉሡ ይልቁንም አልፎአልፎ የምናስተውላቸው ድርጊቶች የተስፋችንን ጭላንጭል የማጨለም፤ እርምጃችንን የመግታት እና ወደ ኋላ የመጎተት አደጋ እየደቀኑናቸው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚያ የከፋው የግጭት፣ የሁከት እና የብጥብጥ ጊዜ እንኳን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የራስን ንብረት የማውደም እና በርካታ
ተሽከርካሪዎችን የማቃጠል እርምጃዎች ተወስደዋል::
አሁን እንደጀመርነው አይነት ማህበረሰባዊ ለውጥ በራሱ የህዝብን መነሳሳት እና ፈጣን እርምጃን፤ እንዲሁም ከወትሮው የተለየ ስነልቡና እና እንቅስቃሴ ይዞ የሚመጣ ሂደት ነው ይላሉ አቶ ንጉሡ።
በመሆኑም ስክነት፣ ብልህነት፣ አስተዋይነት እና እርጋታ ካልታለበት፣ ለውጡም ላይሳካ፤ የለውጥ ኃይሎችንም ለፀረለውጥ ሀይሎች ሰይፍ ሊዳርግ ይችላልና ታላቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል።
የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አክለውም፦“በክላልችን ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ብቻ የለውጡን ወቅት የማይመጥኑ፤ ውዱንየሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ንብረት ያወደሙ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ክስተቶች ተከስተዋል፤ የንግድ ስርዓቱን የሚያስተጏጉሉ እናየአርሶ አደሩ ምርት ጭምር ወደ ፈለገበት ቦታ እንዳይጏጏዝ የሚያደርጉ እንቅፋቶች ተስተውለዋል” ብለዋል።
“ለውጡን ለመቀልበስ አቅደው እና አልመው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ወገኖች የተጠናከረ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጀምረዋል “ያሉት አቶ ንጉሡ፤ “እኛም እነሱ ባጠመዱት ወጥመድ እየገባን እጃችን የገባውን የለውጥ ተስፋ በማጨለም እየተባበርናቸው እንገኛለን “ ሲሉ ወቅሰዋል።
“ሄደን ሄደን ሰሞኑን ሻሸመኔ ላይ ያየነው የጭካኔ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሰናል ፡ ፡ በክልላችንም አሁን የሚታዩት ምልክቶች ይህንን ዓይነትክስተት ይዘው ላለመምጣታቸው ምንም ዋስትና የለም ፡ ፡” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ስለሆነም፣ እንደ አቶ ንጉሡ ገለጻ፣ መደማመጥ፣ መስከን፣ ማስተዋል፣ መረጋጋት እና ለህግ የበላይነት መገዛት ወቅቱ የሚፈልጋቸው ጉዳዮችሲሆኑ ስሜታዊነት፣ አሉባልታና ግርግር ልንርቃቸው የሚገባ የለውጡ እንቅፋቶች ናቸው ፡ ፡ ሃሳባቸውን ሲቋጩ፦”ወጣቶች ይህንን በመገንዘብ የህግ የበላይነት እንዳይጣስ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ንጉሡ “የፖሊስን ስራ ለፖሊስ በመተው የአጋርነት ሚናችሁን መወጣት
ይገባችኋል “ብለዋል።