በኬንያ ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትዕዛዝ በርካታ ስቃይና በደል እየደረሰባቸው መሆኑ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 11/2010)በኬንያ ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትዕዛዝ በርካታ ስቃይና በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች አጋለጠ።

የሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ተመራማሪ ፍሌክስ ሆርን እንደገለጹት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ረጅም እጅ ባላቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አማካኝነት በኬንያም እየኖሩ ይገረፋሉ፣ከፍተኛ ስቃይም እየደረሰባቸው ይገኛል።

በተለይ በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኬንያ ፖሊሶችን በገንዘብ እየደለለ ስደተኞቹን አሳስሮ ወደ ሀገር ቤት በግዴታ እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑንም ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ኑሮ በኬንያ ስቃይና መከራ ሆኖባቸዋል።

እስራትንና ግድያን ፈርተው ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ግፍ ተከትሏቸዋል።

ወደ ናይሮቢም መግባቱን የሒዩማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ ፍሌክስ ሆርን ገልጿል።

እንደ ሰብአዊ መብት ተመራማሪው ገለጻ በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለስልጣናት የኬንያ ፖሊሶችን በገንዘብ እየደለሉ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እንግልትና በደል እንዲያደርሱ እያደረጉ ናቸው።

በዚህም ኢትዮጵያውያኑ የስደተኝነት መብታቸው ተጥሶ ይገረፋሉ፣ይታሰራሉ ከዚህም አልፎ በግዳጅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ።

ይህ ብቻ አይደለም የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በመሆናቸው ከኬንያ ተላልፈው ለኢትዮጵያ አገዛዝ እንደሚሰጡም ፍሌክስ ሆርን ይናገራል።

እንዲህ አይነቱ ኢትዮጵያውንን አሳዶ የማሰርና የማንገላታት ስራ በኬንያ ብቻ የተወሰነ አይደለም ብሏል ፍሌክስ ሆርን።

ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በሱዳን፣በዩጋንዳ፣በጅቡቲ፣በየመንና በመሳሰሉት ሀገራትም ተመሳሳይ ችግር እንደሚገጥማቸው የሒዩማን ራይትስ ዎች ተመራማሪው ገልጿል።

ከዚህ ቀደም የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ታፍነው መወሰዳቸውን፣የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው ኦኬሎ አኳይ፣ከሶማሊያም የኦብነጉ ከፍተኛ አመራር አብዲከሪን ሼክ ሙሴ በሃይል ታግተው ወደ ኢትዮጵያ መተላለፋቸውንም ፍሊክስ ሆርን አስታውሰዋል።

እንዲህ አይነቱ ኢትዮጵያውያንን በተሰደዱበት ሀገር ተከትሎ የሰብአዊ መብት ጥሰት ማድረስ በአለም አቀፍ ህግ የተከለከለ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ይገልጻል።

እናም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በሀገራቸው አገዛዝ ከሚደርስባቸው ስቃይና በደል እንዲታደጋቸውና ጠንክሮ እንዲሰራ የሒዩማን ራይትስ ዎች ተመራማሪው ፍሌክስ ሆርን ጥሪ አቅርቧል።