(ኢሳት ዲሲ –ጥር 24/2010)
የኬንያ መንግስት በሀገሪቱ ሶስት የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ የወሰደውን ርምጃ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አገደ።
የተቃውሞ ፓርቲ መሪና እጩ ፕሬዝዳንት የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት መሾማቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ ለጣቢያዎቹ መዘጋት ምክንያት እንደሆነም ይታወቃል።
ባለፈው ማክሰኞ በኬንያ ናይሮቢ ኡሁሩ ፓርክ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ሰይመው ቃለ መሃላ የፈጸሙት ሚስተር ራይላ ኦዲንጋ የሀገር ክህደት መፈጸማቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹን የኬንያ መንግስት የዘጋውም ይህንን የራይላ ኦዲንጋን የቃለ መሃላ ስነስርአት ለመዘገብ በመዘጋጀታቸው እንደሆነም ታውቋል።
ኤን ቲቪ፣ሲትዝንና ኬ ቲ ኤን በተባሉት ሶስት ግዙፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ መንግስት በወሰደው ርምጃ የሶስቱም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርጭት ተቋርጧል።
የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ አቤቱታ የቀረበለት የኬንያ ፍርድ ቤት በጣቢያዎቹ ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ትዕዛዝ ሰቷል።
እገዳው ለ14 ቀናት እንዲነሳ ውሳኔ ያሳለፈው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት የመንግስትን ምላሽ ካደመጠና ሁለቱን ወገን ካከራከረ በኋላ ዘላቂ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ጣቢያዎቹ ስራቸውን እንደሚጀምሩና መንግስትም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብር ይጠበቃል።