በኬንያ ወንዶች ተጨማሪ ሚስቶች እንዲኖራቸው የሚያዘው ህግ በፓርላማው ጸደቀ

መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለአመታት ሲያወዛግብ የነበረው ወንዶች ባለ ብዙ ሚስቶች የሚያደርጋቸው ህግ ትናንት በፓርላማ አባላት ሲጸድቅ፣ 30 የሚሆኑ ሴት የፓርላማ አባላት ክርክሩን ረግጠው ወጥተዋል።

አንድ የፓርላማ አባል ” ይህ አፍሪካ ነው፣ በአፍሪካ ባህል የአፍሪካ ሴት ስታገባ ፣ ባለቤትህ ሌሎች በመምጣት ላይ ያሉ ሁለት ወይም ሶስት ሴቶች እንዳሉ ታውቃለች፣ ምንም አዲስ ነገር የለውም” ብለዋል።

አብዛኞቹ ወንድ የፓርላማ አባላት ህጉን የደገፉት ሲሆን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ካጸደቁት የአገሪቱ ህግ ሆኖ ይወጣል።

ከዚህ ቀደም አንድ ባል ተጨማሪ ሚስት መያዝ ካሰበ ሚስቱንና ቤተሰቡን ማማከር የሚኖርበት ቢሆንም፣ በአሁኑ ህግ ግን ቤተሰቡን ሳያማክር ተጨማሪ ሚስት እንዲያገባ ተፈቅዶለታል።

በአዲሱ ህግ መሰረት ወንዶች ሚስቶቻቸውን ሲፈቱ 30 በመቶ የሚደርሰውን ሃብታቸውን ብቻ የማካፈል ግዴታ ተጠሎባቸዋል።

ማንኛውም የኬንያ ወጣት እድሜው 18 አመት ከመሙላቱ በፊት ሚስት የማግባት መብት እንደሌለው በህግ ተደንግጓል።