በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግጭት የሚፈጥሩ አካላት አሉ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 14/2011) የውጭ አጀንዳ ወይም ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግጭት የሚፈጥሩና የሚያውኩ አካላት እንዳሉ የሳይንስና ክፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሃገሪቱ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ግጭቶች መፈጠራቸው ታውቋል።

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  የግለሰቦች ግጭት ወደ ቡድን ወይም አካባቢ ወስዶ በተደራጀ ሁኔታ ተማሪዎችን ማጋጨት በምንም መንገድ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል፡፡

‘’ወደ አማራ ክልል የሚመጡ የየትኛውም አካባቢ ተማሪዎች የአማራ ልጆች ናቸው፡፡›› ብለዋል አቶ ገዱ።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ አመንቴም ለተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

‘’ ማንም ከየትም ሆኖ በሚፈጥርልህ በውል  እንኳን በማይታወቅ ምክንያት ሌላውን አታጥቃው’’ ብለዋል ዶክተር ታደሰ።

አሶሳ ሰሞኑን የተማሪዎች ግጭት ማዕከል ሆና ቆይታለች።

3 ተማሪዎች ህይወታቸው ያለፈበት የሶሳ ዩኒቨርስቲው ግጭት አሁን ላይ ጋብ ማለቱ ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በአሶሳው ግጭት ከተገደሉት ሶስት ተማሪዎች በተጨማሪ 34 ተማሪዎች ተጎድተው ሆስፒታል ገብተዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ‘’አሁን ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ለማደናቀፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ዒላማ ያደረገ የሁከት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው’’ ሲሉ ገልጸዋል።

የአሶሳውን ግጭት ተከትሎም በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ግጭቶች መፈጠራቸውን የገለጸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቀድሞው በተለየ መልኩ ዩኒቨርስቲዎችን ኢላማቸው አድርገው ለውጡን ለማደናቀፍ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው ብሏል።

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተነሳው አለመረጋጋትን በምሳሌነት የጠቀሱት ዶክተር ሂሩት ተማሪዎችን ለብጥብጥ ያነሳሳው ምክንያት ሲጣራ ውሸት ሆኖ መገኙቱን አስረድተዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲም ተመሳሳይ ግጭት የተከሰተ ሲሆን በአሶሳ ዩነቨርስቲ ከተገደሉት ተማሪዎች አንዱ የአማራ ተወላጅ በመሆኑ ግጭቱ እንዲነሳ እንዳደረገ ተገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ፖሊስ ሃይል መጠቀሙን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመልክታል።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው የግጭት አዝማሚያ ጥሩ አይደለም የሚሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የግለሰቦች ግጭት ወደ ቡድን ወይም አካባቢ ወስዶ በተደራጀ ሁኔታ ተማሪዎችን ማጋጨት በምንም መንገድ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል፡፡

ችግሩ የተለየ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው እና አሁን እየተፈጠረ ያለው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ያላስደሰታቸው አካላት በታቀደ መንገድ የሚያራምዱት የግጭት ሴራ ነው ያሉት አቶ ገዱ ተማሪዎችም ስሜታዊ በመሆን የሌሎች አጀንዳ ፈፃሚዎች ሳይሆኑ ችግር ፈጣሪዎችን አጋልጠው እንዲሰጡ አቶ ገዱ ጠይቀዋል።

አቶ ገዱ ወደ አማራ ክልል የሚመጡ ተማሪዎች የየትኛውም አካባቢ ተማሪዎች የአማራ ልጆች ናቸውም ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ አመንቴ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚደረገውን ግጭት በማውገዝ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዶክተር ታደሰ ‘’አጠገባችሁ ያለው ተማሪ ወንድማችሁ እንደ እናንተው ከምስኪን ቤተሰብ የተገኘ፣ ጭራሮ ለቅማ ጠላ ሸጣ ጉሊት ቸርችራ ወይም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የመንግስት ስራ የምትኖር እናት የላከችው ነው።

እናም ማንም ከየትም ሆኖ በሚፈጥርልህ በውል እንኳን ተለይቶ በማይታወቅ ምክንያት ብለህ አታጥቃው ብለዋል ሰሞኑን በዩንቨርሲቲው በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ።