የደቡብ አቸፈር አመራሮች በሕዝብ ተቃውሞ ከሃላፊነታቸው ተነሱ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 14/2011) በአማራ ክልል የደቡብ አቸፈር ወረዳ አመራር አባላት በሕዝብ ተቃውሞ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደረገ።

ቁጥራቸው 42 ይሆናል የተባለው የወረዳው አመራር አባላት ከለውጡ ጋር የማይሄዱ ስልጣን ይዘው ሕዝቡን ሲበድሉ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

የወረዳው ዋና ከተማ ዱርቤቴ ወደ ከተማ አስተዳደርነት እንድትሸጋገር ይዞን አስተዳደሩም ከፍኖተሰላም ወጥቶ ወደ ባህርዳር ምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲዛወርም ሕዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቋል።

የደቡብና ሰሜን አቸፈር ሁለት ወረዳዎች ትርፍ የግብርና ምርት አምራቾች በመሆናቸው ለክልሉ መንግስት ከፍተኛ ግብር በመክፈል ይታወቃሉ።

በሁለቱ ወረዳዎች ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የሕዝብ በደል እንዳለ ኢሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።

በአንድ አስተዳደር ስር የነበሩት ሁለት የሰሜንና የደቡብ አቸፈር ወረዳዎች በሁለት ተከፍለው በአስተዳደር ካቢኔ አባላት ችግር አካባቢውን ከማልማት ይልቅ ሕዝቡን መበደላቸው የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሷል በተለይ ደግሞ በደቡብ አቸፈር የዱርቤቴ ከተማ ነዋሪዎች ጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘቱ አደባባይ በመውጣት የወረዳው አመራር አባላት እንዲወርዱ ጠይቀዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ አቶ ጸጋዘአብ መርሻ ለኢሳት እንደገለጹት ሕዝቡ በለውጥ አደናቃፊዎች በመማረር ላይ ይገኛል።

እንደ ነዋሪው ገለጻ የደቡብ አቸፈር ወረዳ አመራር አባላት በዘመድ አዝማድ የተሳሰረና ጥቅም ያገናኛቸው ሰዎች ያሉበት ነው።

እናም የወረዳው ሕዝብ አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል ነው ያሉት።

ይህንኑ የሕዝብ ጥያቄ ተከትሎም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/የወረዳ አመራር አባላቱን ማንሳቱንና ሕዝቡ ይሰሩልኛል ያላቸውን ሰዎች እንዲመርጥ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የደቡብ አቸፈር ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለስ ገድፍ የሕዝቡን ጥያቄ ተገቢነት ለኢሳት በሰጡት መግለጻ አረጋግጠዋል።

እናም ለውጡን ከዳር ለማድረስና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አዴፓ ዝግጁ ነው ብለዋል።

በዚሁም መሰረት ሕዝቡ ሁሉንም የደቡብ አቸፈር ወረዳ አመራር አባላት አንፈልግም በማለቱ በገዛ ፈቃዳቸውም ሆነ በአዴፓ ውሳኔ ከሃላፊነት እንደተነሱ አረጋግጠዋል።

በደቡብ አቸፈር የዱርቤቴ ከተማ ሕዝብ ወረዳቸው በፍኖተሰላም ዞን ስር በመሆኑ የአዊ በሔረሰብ ዞንን ተሻግረን በመሄድ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት በመዳረጋችን ባህርዳር በሚገኘው የምዕራብ ጎጃም ዞን ስር እንተዳደር ሲሉም ጠይቀዋል።

የዱርቤቴ ከተማ በከተማ አስተዳደር ስር እንድትዋቀር በመጠየቅም በከንቲባ ደረጃ እንድትመራም ጠይቀዋል።

በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በአግባቡ እንዳልተሰሩና ሌሎች የልማትና የማህበራዊ ችግሮችም እንዳልተፈቱ ነዋሪዎቿ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።