(ኢሳት ዲሲ–የካቲት17/2011)በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና በአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ስራአስፈጻሚ አባላት መካካል በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ባሉ ችግሮች ላይ ውይይት መካሄዱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
የሁለቱም ፓርቲ ስራ አስፈጻሚዎች ውይይት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ከተካሄደ በኋላ ችግሮችን ገምግመው ለውጡን በይበልጥ ለማስቀጠል የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ኦዴፓና አዴፓ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሉ ችግሮች ላይ መክረውም ከተማዋን በጋራ ለመምራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በኢሕአዴግ ወስጥ ጥልቅ ተሀድሶ መካሄዱን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ሲለቁ ግንባሩ የድርጅቱን አመራሮች ለመለወጥ ባደረገው ሂደት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማሳየት ሕወሃትን ከፖለቲካ አገዛዝ መንበሩ እንዲለቅ ማስቻላቸው ሲነገር ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንዲመጡም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ፓርቲያቸው አዴፓ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል።
ለውጡ እውን ከሆነ በኋላ ግን ሁለቱ ፓርቲዎች መተጋገዛቸውን ቢቀጥሉም በስልጣን አመዳደብ እና በአሰራር ግድፈቶች የተነሳ በመሃላቸው ንፋስ ሳይገባ አይቀርም የሚሉ ወስጥ አዋቂ ምንጮች አሉ።
በኦዲፓ የሚመራው የለውጥ ሃይል የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ ወዲህ በአዲስ አበባ ከንቲባ አመዳደብና ምርጫ ላይ የፖለቲካ ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበርም ይነገራል።
ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የለውጡ አካል ናቸው ከሚባሉት አንዱ ዶክተር አምባቸው መኮንን በፓርቲያቸው አዴፓ አማካኝነት ታጭተው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይሁንታ ካገኙ በኋላ በኦሮሞ ዴሞክራሲያው ፓርቲ በኩል ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ በኦሮሞ ልትመራ ይገባታል በማለታቸው የዶክተር አምባቸው ምደባ እንዲቀር መደረጉም ነው የሚገለጸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ላይ ልዩነት ተፈጥሮ ቢቆይም አዴፓ ለውጡ እንዲጠናከር ባለው ፍላጎት ምክንያት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ከተማዋን እንዲያስተዳድሩ እና አዴፓም ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስን በምክትልት እንዲሰየሙ ፈቅዶ ሁለቱም ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን በወቅቱ ለማስወገድ ችለዋል።
ከለውጡ በኋላ በፌዴራል ደረጃ በነበረው የካቢኔ ሹመትና በመንግስት የስልጣን እርከኖች ያለይሉኝታ ገንዘብና ስልጣን ባለበት ቦታ ሁሉ እየተመዳደቡ ነው በሚል ሲታሙ የቆዩት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) አመራሮች የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን እና ሊሎችንም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ገሸሽ አድርገዋል ተብለው ሲተቹም ነበር።
ይሕ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ስራአስፈጻሚ አባላት የለውጥ ሂደቱን በተመለከተ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ግምገማ አካሂደዋል የተባሉት።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንዳሉት ከእያንዳንዳቸው ፓርቲዎች ዘጠኝ ስራአስፈጻሚዎች በጠቅላላው 18 አባላት በተገኙበት በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ባሉ ችግሮች ላይ ሰሞኑን ውይይት አካሂደዋል።
የሁለቱም ፓርቲዎች ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተካሄደ በኋላ ችግሮችን ገምግመው ለውጡን በጋራ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታወቋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሉ ችግሮች ላይ መክረውም ከተማዋን በጋራ ለመምራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ በአዲስ አባባ በተለይም በክፍለ ከተሞችና በወረዳዎች የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ከመታወቂያ አሰጣጥና ያልተጋባ ነገር ከማድረግ ጋር በተያየዘ የከተማዋን ሕዝብ እንዲመሰቃቀል ተደርጓል።
በክፍለ ከተሞችም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሚና በዝቶ በመታየቱ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ጥያቄ በማንሳታቸው አሰራሩ እንዲስተካካል መስማማታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በኢንጂነር ታከለ ኡማ የአመራር ሁኔታን በተመለከተ ግምገማ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው በአዴፓ የተሾሙት አቶ እንዳወቅ አብጤ ከኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር ሁኔታውን በመተጋገዝ እንዲያስተካክሉ መመሪያ መተላለፉንም ምንጮች ገልጸዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሁለቱ ፓርቲዎች ግምገማ በኋላ አዴፓ ከአዲስ አበባ ከተማ ካድሪዎቹ ጋር ተወያይቷል።
በዚሁ ጊዜም አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እንዳወቅ አብጤ አዲስአበባ የነዋሪዎቿና የአፍሪካ መዲና እንጅ የማንም አይደለችም የለም መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላም በአሁኑ ጊዜ የአዴፓ እና የኦዴፓ የጋራ ትብብር ከግምገማው በኋላ ይበልጥ መጠናከሩ ይነገራል።
ሕወሃት አሁን ባለው የሃይል አሰላለፍ በኦዴፓና አዴፓ መካከል ልዩነት በመፍጠር የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ እንዲጋጭ ፍላጎት እንዳለው የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ።
በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከልም አሁንም ያልጠራ የሀሳብ ልዩነት መኖሩም ይነገራል።