በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ዜጎች በጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሰመጉ አስታወቀ።

ታኀሳስ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የመንግስት ያልተመጣጠነ የሃይል እርምጃ፣ ከመነሻው ሰላማዊ የነበረውን ተቃውሞ ግብታዊ መልክ እንዲይዝና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንዲባባስ በማድረግ ለዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳት እና የህዝብ እና የግል ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ሲል ድርጅቱ ገልጿል።
ሰመጉ ታህሳስ 11 ቀን 2008 ዓም ” ከአዲስ አበባና የኦሮምያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ይቁሙ”በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፣ ከህዳር 2008 ዓም መጨረሻ ጀምሮ የአዲስ አበባና ኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞችን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም በምእራብና በደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ በፊንፈኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ከተሞች፣ በምእራብ ወለጋ፣ በአርሲ፣ በባሌ እና በምስራቅና በምእራብ ሃረርጌ እንዲሁም በሌሎችም የኦሮምያ ዞኖች በሚገኙ በርካታ ከተሞች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን አስታውሷል።
ማስተር ፕላኑ በህዝብ ላይ መፈናቀል ያስከትላል የሚል ጥርጣሬ እና ስጋት ገባቸው ዜጎች ተቃውሞአቸውን ስርአት ባለው መንገድ በሰላማዊ ሰልፍ የሚገልጹበት ሁኔታ በመንግስት ባለመመቻቸቱ ፣ ከግቢያቸው ሳይወጡ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን በገለጹና ተቃውሞአቸውን ባሰሙ ተማሪዎች ላይ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት አላስፈላጊ የሃይል እርምጃ ቀውሱ አሁን ለደረሰበት አስከፊ ደረጃ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲል ለደረሰው ጥፋት መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።
የመንግስት ያልተመጣጠነ የሃይል እርምጃ ከመነሻው ሰላማዊ የነበረውን ተቃውሞ ግብታዊ መልክ እንዲይዝና ሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንዲባባስ በማድረግ ለዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳትና የህዝብና የግል ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት መንገዶች በመዘጋታቸው በአንዳንድ የደቡብ ምእራብ ሸዋ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረው የብሄር ግጭት በወቅቱ ለማብረድ እና ዜጎችን ከግድያና ንብረት መውደም ለመታደግ አስቸጋሪ በማድረጉ ተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ማድረጉን ድርጅቱ ገልጿል።
መንግስት ሽብረተኞች ባላቸው በጸጥታ ሃይሎች ላይ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ዜጎች በጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑና በቁጥጥር ስር የዋሉት ዜጎች እጣ ፋንታ ድርጅቱን እንደሚያሳስበው ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታህሳስ 8 ፣2008 ዓም በአወዳይ በነበረው ተቃውሞ አንድ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ቆስላ ህይወት ፋና ሆስፒታል ከገባች በሁዋላ ህይወቷ ማለፉ ታውቋል። ሌላ ወጣት ልጅም እንደዚሁ በጥይት መቁሰሉን ተከትሎ ህክምና ሲያገኝ ከቆየ በሁዋላ መሞቱን ለማወቅ ተችሎአል። የሁለቱ ታዳጊዎች የቀብር ስነስርዓት መፈጸሙን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል።
በሃረር በተደረገው ስብሰባ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣኖች “ግጭቱን የሚያነሳሱት የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ናቸው፣ ማስተር ፕላኑም ቆሟል” በሚል ከተናገሩ በሁዋላ ህዝቡ ሃሳቡን እንዲሰጥ ጋብዘውታል።
ተሳታፊዎቹ እየተነሱ የተለየዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፣ አንደኛው ተናጋሪ ይህን ስብሰባ ቀድሞ ማካሄድ ሲገባ አሁን ህዝብ ከተገደለ በሁዋላ ማድረጋችሁ ተገቢ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ” ችግሩ ከአምባገነንነት የመጣ ነው። እና ብንናገር ምንም አናመጣም፤ ብንናገርም ህዝቡ የሚለውን ስለማታዳምጡ ትርፍ የለውም” ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ህዝቡ ወደ አደባባይ የወጣው በማስተር ፕላኑ ብቻ ሳይሆን በመልካም አስተዳደር ችግር ጭምር ነው፣ መሬት እየቸበቸባችሁ ነው፤ ወጣቱን ያዝሉን ትላላችሁ፣ እናንተ ወጣቱን በዘር እየከፋፈላችሁ ስራ እያሳጣችሁት ነው፤ ወጣቱን የምትይዙት እናንተ ናችሁ፣ ልጆቻችን ተምረው ለሃሽሽ፣ ተምረው ለሲጋራና ለጫት የሆኑት በእናንተ ምክንያት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላው ተናጋሪ ደግሞ እኛ አንድ ነን፣ አንድ አዳምና ልጆች ነን፣ ሽንኩርትና ድንች የሚበቅለው በአንድ መደብ ላይ ነው። እኛም የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደዛ ነን፤ የምትለያዩንና የምታጋጩን እናንተ ናችሁ፤ እርስ በርስ ማጋጨታችሁን አቁሙልን” ብለዋል።
ሰብሳቢውም ” የመልካም አስተዳደር ችግሩ አገራዊ በሽታ ነው፤ ችግሩን ለመፍታት በ2008 ዓም ጀምረን ነበር፤ አሁን ይህ ችግር ጣልቃ ገብቶብ አደናቀፈን፣ ስለዚህ ይህ የጸጥታ ችግር በመነሳቱ ስራችንን መስራት አልቻልንም።” ሲሉ ህዝቡ ግጭቱን እንዲያቆም ጠይቀዋል።
ምንጮች እንዳሉት በየክልሎች የሚገኙ የህወሃት አባላት ለብቻው እየተጠሩ ራሳቸውን በልዩ ሁኔታ እንዲጠብቁና ማንኛውንም እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ለጸጥታ ሃይሎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል።
መንግስት በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል መቆጣጠሩን ቢገልጽም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ውጥረቱ እንዳለ ነው።
መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ታህሳስ 17 በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል።መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ላይ የወሰደው እርምጃ እንዲሁም ለሱዳን በሚሰጠው መሬት ዙሪያ ህዝቡ የተቃውሞ ድምጹን ያሰማል ተብሎ ይጠበቃል።