ታኀሳስ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት ከባድ ማስጠንቀቂያ በሰጠ ማግስት በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች መንግስትን የሚቃወሙ ህዝባዊ አመጾች ተካሂደዋል። ህዝባዊ አመጾቹ በሃረርጌ አሰቦት፣ በምእራብ ወለጋ ባቡ ገምበሌና ነጆ፣ በሆድሮጉድሩ በጋጨቲ እንዲሁም በአሰላ የተካሄዱ ሲሆን፣ በቡራዩ ፣ አምቦና አወዳይ ከተሞች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ተሰማርተው ቅኝት እያደረጉና የሚጠረጥሩት ወጣት እየያዙ እያሰሩ ነው።
ታህሳስ 5 በአወዳይ የነበረውን ተቃውሞ በማስመልከት ዘጋቢያችን ከቦታው ያጠነከረው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣የጫት እና ሌሎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ይዘው የመጡ አርሶደአሮች በወታደሮች ተደብድበው ታስረዋል። ህዝቡ በተቃውሞው ወቅት ተይዘው በአወዳይ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች እንዲፈቱ ያደረገ ሲሆን፣ ከእስር ቤት ጠባቂ በተተኮሰ ጥይት ሶስት እስረኞች ቆስለዋል።ህዝቡ ቁስለኞችን ይዞ ወደ አብዲ በሽር መካከለኛ ክሊኒክ ሲወስዱዋቸው፣የክሊኒኩ ባለቤት ከመንግስት የሚደርሰውን ጥቃት በመፍራት አላክምም በማለታቸው የክሊኒካቸው መስታውት በተበሳጩ ወጣቶች ተሰብሯል። ግለሰቡ ለህብረት ባንክ ያከራዩት ፎቅ መስታውትም የተሰበረ ሲሆን፣ ባለሀብቱም ግንባራቸው በድንጋይ ተፈንክተዋል።
ህዝቡ መንግስትን ከመቃወም ውጭ እርስ በርስ የነበረው መከባበር አስገራሚ እንደነበር ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
በኦሮሚያ ከተሞች እየተቀጣጠለ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በአዲስአበባም ሊቀጥል ይችላል በሚል ስጋት የጸጥታ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠብቋል፡፡ ወረዳዎችም ሕዝቡን እየሰበሰቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲመካከሩም ከአ/አ አስተዳደር ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡
በአዲስአበባ ጎዳናዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ዱላ እና ክላሽ የያዙ ፖሊሶች በብዛት የተሰማሩ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ደርጅቶች ጥበቃቸው ተጠናክሮአል፡፡ በብዙ የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ ጫማ የሚጠርጉ ሊስትሮወች ሳይቀሩ አንዳች የተለየ እንቅስቃሴ ሲያዩ ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የኦሮሚያን ተቃውሞ በጠመንጃ ሃይል ለመቆጣጠር ባለፈው አንድ ሳምንት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ተቃውሞን ከመቆጣጠር ይልቅ በተቃራኒው እየተባባሰ መምጣቱ የአገዛዙን መሪዎች አስደንግጦአል፡፡
የመብራት እና ኢንትርኔት መስመር መቆራረጥ እጅግ ተባብሶ ቀጥሎአል።ከአዲስአበባ በተለያዩ ወረዳዎች አመራሮች በስብሰባ የተወጠሩ ሲሆን ሕዝቡንም በየአዳራሹ እየሰበሰቡ እንዲያወያዩ በታዘዙት መሰረት ስራቸውን ማከናወን ጀምረዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞው ወደ ህዝባዊ አመጽ መሸጋጋሩን አስታውቋል።