(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 19/2009) በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተነገረ።
በምዕራብ ኦሮሚያ በበርካታ አካባቢዎች የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች የንግድም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም። በምዕራብ አርሲ ከሻሸመኔ እስከ ባሌ ሮቤ ያለው መስመር ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኗል።
የኦሮሚያው አድማ በአማራ ክልል የትራንፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ በማድረግ ለ3ኛ ቀን መቀጠሉም እየተነገረ ነው።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ወጣቶች በተደራጀና ሀገር አቀፍ በሆነ መልኩ የሚጠራ አድማ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው ተብሏል።
በምዕራብና በምስራቅ ሀረርጌ አወዳይ፡ ገለምሶ፡ መኢሶ ዛሬም ሙሉ በሙሉ አድማው ተመቷል።
ወደ ጅጅጋ የሚያመሩ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ቆመዋል። የፌደራል ፖሊሶችን ያሳፈሩ ፓትሮል ተሸከርካሪዎች በቀር በዋና ዋና ሀገር አቋራጭ መንገዶች ላይ የሚታይ መኪና የለም።
በአድማው ምክንያት የጫት ንግድ መቆሙ ታውቋል፡። ወደ አጎራባች ሀገራት የሚላከው ጫትም እንደቆመ መረጃዎች ያሳያሉ። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝባቸው ጫትና ቡና አቅርቦታቸው በመቀነሱ እንዲሁም የንግዱ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ እያሳረፈ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል።
አገዛዙ ችግሩን በሃይል ለመፍታት በማሰብ፣ ወጣቶችን ይዞ እያሰረ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ ነው ተብሏል።
በምስራቅ ሃረርጌ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች መኪኖችን አጅበው ቢጓዙም መኪኖች ግን ከመሰባበር አላመለጡም።
በአወዳይ አንድ በወታደሮች ታጅቦ የሚሄድ መኪና በድንጋይ ሲመታ፣ ወታደሮች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።
በዚሁ ከተማ ነሃሴ 18 2009 ምሽት ላይ ቅኝት ሲያደርግ የነበረ የፖሊስ መኪና ተገልብጦ፣ 3 ፖሊሶች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ሁለት ፖሊሶች ደግሞ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።
በምዕራብ የኦሮሚያ ክልል በተለይ በአምቦ መስመር የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙ ይነገራል። የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ንቅናቄ ማዕከል በመባል በምትጠቀሰው ጊንጪም አድማው ተካሂዷል።
በወለጋም በነቀምት፣ ደምቢዶሎና ሌሎች አካባቢዎች ሱቆችና መደብሮች ተዘግተዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። ተሽከርካሪዎች በፖሊስ አጀብ በሌሊት ለመጓዝ ሙከራ ቢያደርጉም ዛሬ አደጋውን በመስጋት ማቆማቸው ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰበታ፡ ለገጣፎ፡ ቡራዩ፡ ሱሉልታ፡ ሆለታ ምንም ዓይነት የንግድም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም። ከመጀመሪያውና ሁለተኛው ቀን ይበለጥ ዛሬ የተጠናከረ የአድማ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች እንደሚታይ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፡ ዶዶላ፡ አዳባ፡ አሳሳ እስከ ባሌ ሮቤ ያለው መስመር፡ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኗል። በእነዚህ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መታሰራቸው እየተነገረ ነው።
አድማውን ተቀላቅለዋል በሚል የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪዎች መታሰራቸው የተገለጸ ሲሆን የጅምላ አፈሳም የተካሄደባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ታውቋል።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደሚገልጹት አፈሳውና እስሩ ህዝቡን ዕልህ ውስጥ እንዲገባ በማድረጉ ከመጀመሪያዎቹ ቀናት ይልቅ ዛሬ የአድማው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ተካሂዷል።
ከዚሁ ከኦሮሚያ ክልሉ አድማ ጋር በተያያዘ ከባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ዳንግላ፣ ኮሶበር፣ ቻግኒ፣ ግልገል በለስ፣ ፍኖተሰላም፣ ቡሬ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ ፣ ደጀን ወደ አዲስ አበባ የሚሰሩ የህዝብ መጓጓዣ አውቶብሶች በአብዛኛው ስራ ማቆማቸው ታውቋል።
በቅርቡ ከኮሶበር እና ቻግኒ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ስራ የጀመረው እና ንብረትነቱ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸው እንደሆነ የሚነገርለት ጎልደን ባስ ስራ ሊያቆም እንደተገደደ ተሰምቷል።
ሰላም ባስ ፣ አባይ ባስ እንዲሁም ደረጃ 1 አገር አቋራጭ አውቶብሶች ስራ አቁመው ይታያሉ። ከባህርዳር ነቀምቴ ፣ ከቡሬ ወለጋ የሚደረጉ የትራንስፓርት እንቅስቃሴዎች ተቋርጠዋል።
በሌላ በኩል ሀገር አቀፍ በሆነ ደረጃ አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ ከመስከረም ሁለት ጀምሮ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በአማራ ክልል ራሳቸውን ያደራጁ ወጣቶች ገለጸዋል።
በተናጠል የሚደረገውን ትግል ሀገር አቀፍ መልክ ይዞ እንዲካሄድ ስራዎች እየተሰሩም ነው ብለዋል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተካሄዱትና አሁንም እየተካሄዱ ባሉት የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በተለይ ጫትና ቡና ላይ የተመሰረተው የውጭ ንግድ ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል ነው የሚነገረው።
በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ባለው አድማ ዕለታዊ ቀለብና ውሃን ጨምሮ ጫት የምታስገባው ጅቡቲ ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቋ እንደማይቀር የዘርፉ ተንታኞች ይገልጻሉ።