ወደ ካናዳ ሲጓዙ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው የሶስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የቀብር ስነስርአት ነገ ቅዳሜ ይፈጸማል

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 19/2009) ከአሜሪካ ወደ ካናዳ ሲጓዙ በአሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሶስት የአንድ ቤተሰብ አባላት የቀብር ስነስርአት በዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ ነገ ቅዳሜ ይፈጸማል።

ከሳምንት በፊት ነሐሴ 11 2009 በካናዳ አልበርት ግዛት ከመለስተኛ የጭነት መኪና ጋር በተፈጠር ግጭት አባትና እናት ተርፈው ሆስፒታል ሲወሰዱ ሶስቱም ልጆቻቸው በአደጋው ማለቃቸው ይታወሳል።

ብሌን፣ክርስቲያንና እምነት የተባሉት የ16፣የ11 አመትና የ11 ወር ሕጻን ከወላጆቻቸው ጋር ለእረፍት ከአሜሪካ ወደ ካናዳ ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት ረቡእ ነሀሴ 11/2009 ከምሽቱ 12 ሰአት አካባቢ በደረሰባቸው አደጋ ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል።

የልጆቹ እናት ወይዘሮ መሰረት ሽፈራውና አባታቸው አቶ ሰለሞን አዱኛ በሔሊኮፕተርና በተሽከርካሪ ፉትሒል ወደተባለ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ተደርጎላቸዋል።

የሕጻናቱ ወላጆች ከድንጋጤ ከወጡና ጤናቸው ከተመለሰ ከቀናት በኋላም በአደጋው ስፍራ ተገኝተው ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን ሻማ በማብራት ልጆቻቸውን አስበዋል።

ጳጳሱን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የተካሄደውን ስነስርአት ተከትሎ የሕጻናቱ ወላጆች ወደ አሜሪካ ሲያትል ተመልሰዋል።

የሕጻናቱም አስከሬን ወደ ሲያትል ከተመለሰ በኋላ ነገ ቅዳሜ የቀብር ስነስርአታቸው ይፈጸማል።

አስከሬኑን ለመመለስና የቀብር ስነስርአቱን ለማስፈጸም ያስፈልጋል የተባለውን አንድ መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በተሳካ ሁኔታ ማሰባሰብ መቻሉም ተመልክቷል።

ኢትዮጵያውያኑ ከ5 እስከ 1 ሺ 300 የአሜሪካን ዶላር ባደረጉት መዋጮ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ግዜ ድረስ በሶስት ቀናት 94 ሺ 965 የአሜሪካን ዶላር መዋጣቱን ለማወቅ ተችሏል።