በኦሮሚያ ክልል ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ በሚሰጠው ስልጠና የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ለ10 ቀናት ተዘግተዋል።

መስከረም (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናት ለ10 ቀናት በአዳማ ከተማ በአክራሪነት እና ሽብርተኝነት ዙሪያ ስልጠና ሲሰጣቸው ከቆየ በሁዋላ፣ አሁን ደግሞ ስልጠናው ወደ ታች አመራር አባላት በመውረዱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰራተኞች ለ10 ቀናት ያክል ጽህፈት ቤቶቻቸውን ዘግተው ስልጠናውን እየወሰዱ ነው።

ህዝቡ  ጉዳይ ለማስፈጽም ወደ ተለያዩ መስሪያ ቤቶች ሲሄድ ባለስልጣናቱ ስልጠና ላይ ናቸው የሚል መልስ እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው ወደ ወረዳዎች ሁሉ ይዘልቃል ተብሎአል። መንግስት በዚህ ስልጠና ምን ለማግኘት እንዳሰበ አልታወቀም። እስካሁን ድረስ በስብብሰባው ላይ የሚቀርቡት አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው ተሰብሳቢ በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ ብሎ አያስብም። ይህም የመንግስት ባለስልጣናትን ሳያስደነግጥ አልቀረም።

የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በአክራሪነት ለመፈረጅ የሚቀርበው ሀሳብ ዋነኛው የውዝግብ መነሻ መሆኑን ስብሰባውን የሚካፈሉ አንዳንድ ሰዎች ገልጸዋል።