ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያየዘ በአጠቃላይ የወደመው ንብረት ከመቶ ሚሊዮን ብር ስለማይበልጥ ብዙ ጉዳት አልደረሰም ሲሉ አቶ ሃይለማሪያ ደሳለኝ ገለጹ።
ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ይህንን የተናገሩት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ሲሆን፣ በጸጥታ ሃይሎች ስለተገደሉ ሟቾች እንዲሁን ታጣቂዎች ዘረፋ ተፈጸመብን ስላሉት ወገኖች አስተያየት አልሰጡም።
በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጣዩ በሃገሪቱ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያመጣውን ጉዳት በተመለከተ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጉዳቱ አነስተኛ በመሆኑ በኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ አያመጣም ብለዋል። እንዲሁም ከህዝባዊ ዓመጹ በኋላ የኢንቨስትመንት ፍላጎት መጨመሩን ተናግረዋል፥ ከአመጹ በኋላ የኢንቨስትመንት ፍላጎት የጨመረበትን ምክንያት ግን አላብራሩም።
በኦሮሚያ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት በተመለከተ ባደረግነው ምርመራ ጉዳቱ ከመቶ ሚሊዮን ብር አይበልጥም ያሉት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ለተጎጂዎቹ መንግስት ክፍያ እንደሚፈጽም ተናግረዋል።
መንግስት የንብረት ጉዳን በተመለከተ ምርመራ ማካሄዱን ጠ/ሚንስትሩ ቢናገሩም፣ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።
በኦሮሚያ የክልል መንግስት ሃይሎች የሚደረገው ማዋከብ በመቀጠሉና እስራቱም በመጠናከሩ በርካቶች ወደጎረቤት ሃገር በመሰደድ ላይ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።