(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)
በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የክልሉ መንግስትና የክልሉ የጸጥታ ሃይል ሰልፈኞቹን አትንኳቸው በማለት የያዙት አቋም ለሰው ሕይወት ማለፍና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ሲል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች በንብረት ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን በማውረድ አዳዲስ ሽስከ መሾም መድረሳቸውንም ይፋ አድርገዋል።
በፌደራል ፖሊስ በተዘጋጀውና ለአመራሩ በቀረበው በባለ 67 ገጽ ማብራሪያ ላይ እንደተመለከተው ችግሩ በተደጋጋሚ የተከሰተባቸው ቦታዎች አራቱ የወለጋ ዞኖች፣ ሁለቱ የሃረርጌ ዞኖች እንዲሁም ምዕራብና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከዋና ዋናዎቹ መካከል ናቸው።
በእነዚህና በሌሎቹ ዞኖች የተከሰተው ሕገ-ወጥ ሰልፍ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሻገር ምክንያት የሆነው በየአካባቢው አመራርና የጸጥታ ሃይል ችግር ነው ሲል ፌደራል ፖሊስ ከሷል።
“በየአካባቢው የሚገኘው አመራርም ሆነ የጸጥታ ሃይል እነዚህን ሕገ-ወጥ ተግባራት ገና ከጅምሩ ድንጋይ እስካልተወረወረ ድረስ የፈለጉትን ይተንፍሱ” ማለቱ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያመራ ምክንያት ሆኗል ሲል ዘርዝሯል።
ይህም ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።
ጉዳቱም ከሰላማዊ ሰዎች አልፎ በፌደራል ፖሊስና በሌሎች የጸጥታ ሃይሎችም ላይ ጉዳት ማስከተሉን ሪፖርቱ ይዘረዝራል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተዘጋጀውና ለፌደራል ፖሊስ አመራሮች ለውይይት የቀረበው ሪፖርት በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም ሰሜን ሸዋ ዞን ከሱሉልታ እስከ ገብረ-ጉራቻ 16 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን፣ 18 የቃጅማ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች መሰባበራቸውን እንዲሁም አንድ የጂብሰም ፋብሪካ በከፊል መቃጠሉን ዘርዝሯል።
የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይል ይህንን ዝም ብሎ መመልከቱም ሊወገዝና ሊታረም ይገባዋል ሲል ያሳስባል።
አደባባይ ለተቃውሞ የወጡትን ሰልፈኞች ሁከተኞች በማለት የሚጠቅሰው የፌደራል ፖሊስ ሰነድ አዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኙት ቢሾፍቱ፣ ቡራዩ፣ መቂ፣ ሰበታን ጨምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባንዲራ መውለብለቡንና የፌደራሉ ባንዲራ እየወረደ መቀደዱን ዘርዝሯል።
ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተዘግተው የነበሩ መንገዶችም በዚሁ በፖሊስ የውይይት ሰነድ ላይ ተዘርዝሯል።
ከአዲስ አበባ- ፍቼ- ጎጃም መስመር/ ከአዲስ አበባ- በደሌ- ጎሬ- ጋምቤላ መስመር/ ከአዲስ አበባ- ነቀምት- አሶሳ መስመር/ ከአዲስ አበባ ሀረርጌ- ድሬዳዋ- ሃረር መስመር/ ከአዲስ አበባ- ሞጆ- ሻሸመኔ- ሐዋሳ- ሞያሌ መስመር በተቃውሞው ሳቢያ ተዘግተው እንደነበርም በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
በእነዚህ መስመሮች ላይ ጎማ በማቃጠል፣ በድንጋይ፣ በእንጨት መንገዶችን የመዝጋት ሁኔታ መከሰቱንም ፌደራል ፖሊስ ይዘረዝራል።
አደባባይ ለተቃውሞ የሚወጡት ሲጀመር ከ20ና 30 አይበልጡም። ሆኖም የክልሉ የጸጥታ ሃይል ወዲያውኑ ስለማይበትናቸው ቀስ በቀስ ወደ መቶዎችና ሺዎች እያደጉ ይሄዳሉ በማለት የኦሮሚያን የጸጥታ መዋቅር የሚወቅሰው የፌደራል ፖሊስ የውይይት ሰነድ ለተቃውሞ የሚወጡትን በተመለከተም ዘርዝሯል።
አንደኛ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የቄሮ መዋቅር፣ ሁለተኛ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መዋቅር እንዲሁም ስራአጥ ወጣቶች አልፎ አልፎ የኦህዴድ አባላት እና በዕድሜያቸው ተለቅ ያሉ ሰዎች እንደሚሳተፉ ገልጿል።
አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 16 ዓመት ነው ሲልም በሰነዱ አመልክቷል።
የፌደራሉ መንግስት የትግራይና የአማራን ክልል ግጭት በተመለከተ በፍጥነት ጣልቃ ገብቶ መፍታቱንና የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌን ክልል ግጭት ግን ችላ ማለቱ በተቃውሞው ወቅት ይንጸባረቅ ነበር ሲልም ጠቅሷል።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ተሽከርካሪዎችን እያስቆሙ ፍተሻ እንደሚያደርጉ የሚዘረዝረው የፌደራል ፖሊስ ሪፖርት በነጆ ከተማ በትግራይ ተወላጆች የተያዙ አራት ተሳቢ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ፍተሻ ማድረጋቸውን ለአብነት ይጠቅሳል።
ተሽከርካሪዎቹ መሳሪያ የጫኑ ናቸው በሚል ሰልፈኞቹ ፍተሻ ባደረጉበት ወቅት ተሽከርካሪዎቹ የጫኑት መድሃኒት ሆኖ በመገኘቱ በሰላም እንደለቀቋቸውም አስታውሷል።
በጸጥታ ሃይሎች ላይ በተደረገ ትንኮሳም በምዕራብ ወለጋ ዞን የሁለት ሚሊሻዎችን ዩኒፎርም አስወልቀው ማቃጠላቸውን፣ የኮሚኒቲ ፖሊስ ጣቢያ ማፍረሳቸውን፣ በቄለም ወለጋ ዞን ደግሞ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት መመታታቸውንና በምስራቅ ሃረርጌ ከፖሊስ መሳሪያ መንጠቃቸውን ይዘረዝራል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን በነበረው ተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የባቦ ገምቤል ወረዳ አመራርን በማባረር አራት አዳዲስ የወረዳ አመራሮች መሾማቸውን እንዲሁም በዚሁ ወረዳ አምባሉ ዱላ በተባለ ቀበሌም ሰልፈኞቹ አዲስ አመራር ሰይመው ነባሩን መሻራቸውን የፌደራል ፖሊስ ሰነድ ይፋ አድርጓል።
ለፌደራል ፖሊስ አመራሮች የቀረበው ባለ 67 ገጽ ሰነድ ሲያጠቃልል አሁንም ከቀውስ አልወጣንም፣ የፌደራል ስርዓቱን ለማናጋት የሚደረገው ሙከራ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም እያጋጠመ ነው በማለት የችግሩን ስፋት አስቀምጧል።
ለዚህ መፍትሄው የተጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ ከግብ ማድረስ ነው ሲልም ይቋጫል።