በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ቀጥሏል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 13/2011) በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት መቀጠሉ ተገለጸ።

ተጨማሪ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

ፋይል

በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ በአሉባልታ በመንዳት ለግጭት የሚዳርጉ ሃይሎች መኖራቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን ጸጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋጋሪ ቀጄላ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ግጭቱ ከተጠበቀው በላይ እየሰፋ መጥቷል።

ተፈናቃዮቹን ለመመለስ የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ ባለመሆኑ ችግሩ እየከፋ መምጣቱንም ሃላፊው ገልጸዋል።

ግጭቱን እያስፋፉ ነው የተባሉ ሃይሎች እነማን እንደሆኑ ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።

ከአንድ ወር በፊት የጀመረው ግጭት መብረድ እንዳልቻለ ነው ከተለያዩ ምንጮች ለማረጋገጥ የተቻለው።

የሁለቱ ክልሎች የጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች ስብስበባ ተቀምጠው ሲመለሱ በቤንሻንጉል ጉምዝ አመራሮች ላይ የግድያ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ የተጀመረው ግጭት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።

ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ መረጃ የሰጡት የምዕራብ ወለጋ ዞን ጸጥታና ደህንነት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋጋሪ ቀጄላ ግን የግጭቱ መነሻ ምክንያት ሌላ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ምክንያቱ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይን መመረጥ ተከትሎ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ በሚፈልጉትና በሚከለክሉት መካከል በተነሳ ውዝግብ ነው ባይ ናቸው አቶ ዋጋሪ።

ምክንያቱ ላይ ሁለቱ ክልሎች ባይሰማሙም ግጭቱን ለማብረድ በጋራ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውኑ እንደነበረ ይናገራሉ።

ሆኖ ሁኔታዎች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ መምጥታታቸውን አቶ ዋጋሪ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል።

በስም ለመጠቀስ ያልፈልጓቸው ሃይሎች በሁለቱ ክልሎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሽብር ዘመቻ ከፍተው ግጭቱ እንዲባባስ እያደረጉ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ዋጋሪ ከቁጥጥር ውጭ ወደሚሆንበት ደረጃ እንዳይደርስ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

በክልሎቹ አጎራባች አከባቢዎች በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች የተጀመረው ግጭት እየሰፋ በመምጣቱ የመንግስት ሹማምንት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱን ነው ለማወቅ የተቻለው።

አቶ ዋጋሪ ከጀርባ ሆነው ህዝቡን የሚያጋጩት ሃይሎች፡ የቤንሻንጉል ነጻ አውጪ ሰራዊት መጣብህ ብለው ኦሮሞውን ያስፈራራሉ፣ ለቤንሻንጉል ጉምዝ ነዋሪዎች ደግሞ ኦነግ መጥቶብሃል እያሉ ያሸብሩታል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመመለስ የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ያሉት አቶ ዋጋሪ ተጨማሪ ሰዎች በመፈናቀል ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የመከላከያ ሰራዊት፣ ከጊምቢ ተነስቶ በካማሺ ውስጥ ለውስጥ በእግሩ ተጉዞ ለመግባት የተገደደው፣ በአካባቢው ያሉ ታጣቂዎች ተሽከርካሪ ላይ እንደሚተኩሱም ተመልክቷል።

እነዚህ ታጣቂዎች እነማን እንደሆኑ ባይገለጽም የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የኦነግ ሰታዊት እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል። ኦነግ ግን ጉዳዩን አስተባብሏል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን የጸጥታ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋጋሪ ቀጄላ መንግስትን ወቅሰዋል።

ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ወደ ክልሉ ደጋግመው ማስታወቃቸውን ነገር ግን መንግስት የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት አልሰጠበትም ሲሉ አቶ ዋጋሪ ተናግረዋል።