የአማራ ክልል መንግስት የራያንና ወልቃይት ጥያቄዎችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ መፍትሄ አያመጣም አለ

የአማራ ክልል መንግስት የራያንና ወልቃይት ጥያቄዎችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ መፍትሄ አያመጣም አለ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ/ም ) ክልሉ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ “የአማራ ብሔራዊ ክልል ከትግራይ ብሔራዊ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የወልቃይትና ራያ አላማጣ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰላም መታወክ” እየገጠመው መሆኑን ጠቅሷል። በወልቃይት አካባቢ በማንነታችን ብቻ ጥቃት ደረሰብን ያሉ የወልቃይት አማራዎች ተፈናቅለው በጐንደር ከተማ የሰፈሩ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በራያ አላማጣ በተፈጠረው ግጭት በሰው ህይወትም ጭምር ጉዳት መድረሱን የገለጸው ክልሉ፣ በተከሰተው ግጭት በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ሃዘን የተሰማው መሆኑን አስታውቋል።
የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ህገ-መንግስታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡን የገለጸው ክልሉ፣ አሁንም ቢሆን መፍትሄው ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት በማድረግ ህገ-መንግስቱ ላይ በመመስረት መፍትሄ መስጠት እንጂ የሃይል እርምጃ መውሰድ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል በማለት የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል በራያ ተወላጆች ላይ የወሰዱትን እርምጃ ነቅፏል።
“በአንድ ክልል የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ለአጐራባች አካባቢዎች መትረፉ አይቀርምና የሰሞኑ የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ችግር ለክልላችንም ትልቅ የፀጥታ ስጋት ሆኗል” የሚለው የአማራ ክልል አስተዳደር መግለጫ፣ “ አንዳንድ ወገኖች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚፈጠረው ችግር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መክሰሳቸው መሠረት ቢስ ውንጀላ ነው ብሎአል።.
“በአዋሳኝ ክልሎች የሚፈጠረው ግጭት የሌላ ክልል ጉዳይ ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ተሻጋሪነት ያለው ሁላችንንም የሚያውክ የሰላም ጠንቅ ነው” የሚለው የክልሉ መግለጫ፣ “የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ህጋዊና ሰላማዊ ጥረት ሁሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን” ጠቅሶ፣ በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የፌደራሉ መንግስት ሚናውን እንዲወጣም ጠይቋል።.
ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ሰዓት ድረስ በአማራ ክልል መግለጫ ዙሪያ የትግራይ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት የሰጡት መግለጫ የለም። የትግራይ ክልል የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ረዳዒ ሃለፎም፣ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ አለማቅረቡንና ጥያቄው የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ያስነሱት መሆኑን ገልጸዋል። ክልሉ በእነዚህ ሃይሎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ባለስልጣኑ ተናግረዋል።