(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2011)በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በሽታውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኙ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን በ11 ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን በ4 ወረዳዎች ፣ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደግሞ በ2 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ተከስቷል፡፡
በሱማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ደግሞ በ8 ዞኖች በሚገኙ 41 ወረዳዎች እንደተከሰተ ነው የተገለጸው።
በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ከ778 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እና በሶማሌ ክልል ከ133 ሺህ ለሚበልጡ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች ለሚገኙ ዜጎች ክትባት እንዲያገኙ የመድሃኒት ወጪ ተደርጓል ተብሏል።
ይህን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቋል።
በዚሁም መሰረት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከአለም ጤና ድርጀት፣ ከአለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ ከህፃናት አድን ድርጀት እና ከኤም ኤስ ኤፍ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን እየመራ እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ ማስታወቁን ኢቲቪ ዘግቧል፡፡
የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኙ ከመቼ ጀምሮና በምን ምክንያት እንደተከሰተ በዘገባው የተጠቀሰ ነገር የለም።