በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ በመፈናቀል ላይ መሆናቸዉን በመግለፅ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል መግለጫ አወጣ

የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ ዜጎች በኢትዮጵያ መንግስት በሃይል ከይዞታቸዉ በመፈናቀል ላይ መሆናቸዉን በመግለፅ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል መግለጫ አወጣ 

በጊቤ 3 የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ ስም የኢትዮጵያ መንግሰት በደቡብ ክልል ኦሞ ሸለቆ የጀመረዉ ድሃ አርሶ አደሮችን ከይዞታቸዉ የማፈናቀል ተግባር አካባቢዉን የሸንኮራ አገዳና የዕፅዋት ነዳጅ ተክል ለሚያመርቱ የአዉሮፓና የሕንድ ከበርቴዎች ለመስጠት ተጠናክሮ መቀጠሉን አለምአቀፍ ድርጅቱ ያወጣዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ይገልጻል።

243 ሜትር ከፍታ ከሚኖረዉ የጊቤ 3 ግድብ ግንባታ በተጨማሪ ለዉጭ ኢንቬስተሮች እርሻ የመስኖ ዉሃ አግልግሎት ለሚሰራዉ 140 ማይል ርዝመት ለሚኖረዉ ማጠራቀሚያ ግንባታ በሺዎች የሚቆጠሩ አነስተኛ ገበሬዎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁን በአካባቢው በመዘዋወር ባገኘዉ መረጃ ማረጋገጡን ድርጅቱ አመልክቷል።

“በኦሞ ሸለቆ ሰዎችንና ቁጥቋጦና ጫካዎችን  ማፅዳት ተጀምሯል።የመንግሰት ወታደሮች በአካባቢዉ ተወላጆች ላይ እርምጃ በመዉሰድ ላይ ሲሆኑ፤ የነዋሪዉ  ተቃዉሞ ጨምሯል፡” ይላሉ በአካባቢዉ ቆይተዉ የተመለሱት የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ተመራማሪ።

የመንግስት እቅድ ሰዎቹን እስከ 2012 የአዉሮፓዉያኑ አቆጣጠር ድረስ ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር መሆኑን የገለፁት ተመራማሪ ፤ “ሰዎቹ ረሃብና የምግብ እጥረት ባለባት አገር ዉስጥ እራሳቸዉን ከሚችሉትት መካከል ይገኛሉ፡” በማለት ጠቅሰዋል።

በሸንኮራ አገዳና በዕፅዋት ነዳጅ ተክል እርሻዎቹ ምክንያት ጉዳት ላይ የሚወድቁ 10 ሺህ የሚሆኑ የቦዲ፤ የሙርሲ፤ እና የክዌጉ ጎሳ አባላት እስካሁን መኖራቸዉ ሲታወቅ ፤ መንግስት ብዙ ቦታ በጠረገና ባፀዳ ቁጥር የተፈናቃቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና በአንድ የሸንኮራ አገዳ ፕሮጀክት ብቻ ከ20 እስከ 40 ሺህ ህዝብ ከይዞታዉ ሊነሳ እንደሚችል ድርጅቱ ባወጣዉ ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል።

ሂደቱ በሌሎች አገሮች ዉስጥ ከዚህ በፊት እንደታየዉ ሁሉ ተፈናቃዮቹ ማንነታቸዉን እንደሚያጡና በመንደሮቻቸዉ ወይንም በካምፓቸዉ ዉስጥ በድህነት በመሰቃየት እራሳቸዉን ዋጋ ቢስ አድርገዉ በመቁጠር በለጋሾች ርዳታ እንዲኖሩ ሊገደዱ እንደሚችሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ገልፀዋል።

ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ባወጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በለንደን የሚገኘዉ የኢትዮጵያ መንግሰት የገለፀዉ ነገር እንደሌለ ታዉቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide