ጥር 2 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእኛ መታሰር ዓለም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፕሬስ ነጻነት አፈና ለማወቅ ችሎአል ሲሉ በእስር ላይ የሚገኙት የስዊድን ጋዜጠኞች መናገራቸው ተሰማ
ሲኤን ኤን የማርቲን ሺቢየ እናት የሆኑትን ካሪን ሽብየን አነጋግሮ እንደዘገበው ማርቲን ሽብየና ጆን ፔርሰን የአለም ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፕሬስ አፈና ለመረዳት በመቻሉ፣ ተልኮአቸው መና እንዳልቀረ ይረዳሉ።
“ጋዜጠኞቹ ንጹሀን ናቸው፣ ምንም ወንጀል እንዳልሰሩ ያምናሉ” ያሉት ካሪን፣ እስረኞቹ በኢትዮጵያ የፍርድ ሄደት ተስፋ የቆረጡ በመሆኑ ይግባኝ ላለማለት ወስናዋል።
ጋዜጠኞችን ለመፍታት ያለው ብቸኛ አማራጭ ይቅርታ መጠየቅ ነው የሚሉት የስዊድን ባለስልጣናት፣ ይህ ማለት ግን ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ናቸው ማለት አለመሆኑን ገልጠዋል።
ጋዜጠኞች ጥፋተኞች ነን ብለው ካላመኑ እንዴት ይቅርታ ሊጠይቁ እንደሚችሉ የተገለጠ ነገር የለም። ካሪን ሽበየ በቃልቲ እስር ቤት ውስጥ ስላለው የእስር ቤት ሁኔታም ለሲኤን ኤን ተናግረዋል።
250 የሚደርሱ እስረኞች በሚገኙበት በአንድ ክፍል ውስጥ፣ መኝታ ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ተሰቃይተው እንደነበር ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል።
ጋዜጠኞቹ ከጊዜ በሁዋላ የመኝታ የደረጃ እድገት በማግኘታቸው 90 ሴንትሜትር ስፋት ባላት አልጋ ላይ ለሁለት እንደሚተኙ ተናግረዋል። በአይጥ፣ በጫጫታ እና ማታ ማታ መብራት ባለመጥፋቱም መቸገራቸውን ጋዜጠኞቹ አክለው ተናግረዋል።
የመለስ መንግስት፣ ሁለቱን ጋዜጠኞች ለእስር በመዳረጉ አለም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በገሀድ ለማየት እንዳስቻለው በሚወጡት ዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል።